መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 98
የዳዊት መዝሙር። ለእግዚአብሔር አዲስ ምስጋናን አመስግኑ፥ እግዚአብሔር ተኣምራትን አድርጎአልና፤ ቀኙ የተቀደሰም ክንዱ ለእርሱ ማዳን አደረገ።
2 እግዚአብሔር ማዳኑን አስታወቀ፥ በአሕዛብም ፊት ጽድቁን ገለጠ።
3 ለያዕቆብ ምሕረቱን ለእስራኤልም ቤት እውነቱን አሰበ፤ የምድር ዳርቻዎች ሁሉ የአምላካችንን ማዳን አዩ።
4 ምድር ሁሉ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፤ አመስግኑ፥ ደስ ይበላችሁ፥ ዘምሩም።
5 ለእግዚአብሔር በመሰንቆ፥ በመሰንቆና በዝማሬ ድምፅ ዘምሩ።
6 በዋሽንትና በመለከት ድምፅ በንጉሥ በእግዚአብሔር ፊት እልል በሉ።
7 ባሕርና ሞላዋ፥ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ይናወጡ።
8 ወንዞችም በአንድነት በእጅ ያጨብጭቡ፤ ተራሮች ደስ ይበላቸው፥ በምድር ሊፈርድ ይመጣልና።
9 ለዓለምም በጽድቅ ለአሕዛብም በቅንነት ይፈርዳል።