መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 46
ለመዘምራን አለቃ፤ ስለ ምሥጢር፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር። አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፥ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው።
2 ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፥ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም።
3 ውኆቻቸው ጮኹ ተናወጡም፥ ተራሮችም ከኃይሉ የተነሣ ተናወጡ።
4 የወንዝ ፈሳሾች የእግዚአብሔርን ከተማ ደስ ያሰኛሉ፤ ልዑል ማደሪያውን ቀደሰ።
5 እግዚአሔር በመካከልዋ ነው አትናወጥም፥ እግዚአብሔርም ፈጥኖ ይረዳታል።
6 አሕዛብ ተናወጡ መንግሥታትም ተመለሱ፤ እርሱ ቃሉን ሰጠ፥ ምድርም ተንቀጠቀጠች።
7 የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው፤ የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው።
8 የእግዚአብሔርን ሥራ፥ በምድር ያደረገውንም ተኣምራት እንድታዩ ኑ።
9 እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነት ይሽራል። ቀስትን ይሰብራል፥ ጦርንም ይቈርጣል በእሳትም ጋሻን ያቃጥላል።
10 ዕረፉ፥ እኔም አምላክ እንደ ሆንሁ እወቁ፤ በአሕዛብ ዘንድ ከፍ ከፍ እላለሁ፥ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ።
11 የሠራዊት ጌታ ከእኛ ጋር ነው፤ የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው።