መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 88
የቆሬ ልጆች የምስጋና መዝሙር። ለመዘምራን አለቃ በማኸላት ለመዘመር፤ የይዝራኤላዊው የኤማን ትምህርት። አቤቱ፥ የመድኃኒቴ አምላክ፥ በቀንና በሌሊት በፊትህ ጮኽሁ፤
2 ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትግባ፥ ጆሮህንም ወደ ጩኸቴ አዘንብል፤
3 ነፍሴ መከራን ጠግባለችና፥ ሕይወቴም ወደ ሲኦል ቀርባለችና።
4 ወደ ጓድጓድ ከሚወርዱ ጋር ተቈጠርሁ፥ ረዳትም እንደሌለው ሰው ሆንሁ።
5 ለዘላለም እንደማታስባቸው፥ እንደ ተገደሉና በመቃብር ውስጥ እንደ ተጣሉ፥ በሙታን ውስጥ እንዳሉ የተጣልሁ ሆንሁ፤ እነርሱም ከእጅህ ተለዩ።
6 በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ፥ በታችኛው ጕድጓድ አስቀመጥኸኝ።
7 በእኔ ላይ ቍጣህ ጸና፥ መቅሠፍትህን ሁሉ በእኔ ላይ አመጣህ።
8 የሚያውቁኝን ከእኔ አራቅህ፤ በእነርሱ ዘንድ ርኵስ አደረግኸኝ፤ ያዙኝ፥ መውጫም የለኝም።
9 ዓይኖቼም በመከራ ፈዘዙ፤ አቤቱ፥ ሁልጊዜ ወደ አንተ ጮኽሁ፥ እጆቼንም ወደ አንተ ዘረጋሁ፥
10 በውኑ ለሙታን ተኣምራት ታደርጋለህን? የሞቱትስ ተነሥተው ያመሰግኑሃልን?
11 በመቃብርስ ውስጥ ቸርነትህን፥ እውነትህንስ በጥፋት ስፍራ ይናገራሉን?
12 ተአምራትህ በጨለማ፥ ጽድቅህንም በመርሳት ምድር ትታወቃለችን?
13 አቤቱ፥ እኔ ግን ወደ አንተ ጮኽሁ፤ በጥዋት ጸሎቴ ወደ ፊትህ ትደርሳለች።
14 አቤቱ፥ ነፍሴን ለምን ትጥላለህ? ፊትህንስ ከእኔ ለምን ትሰውራለህ?
15 እኔ ከታናሽነቴ ችግረኛ ለሞትም የቀረብሁ ነኝ፤ ከፍ ከፍ ካልሁ በኋላ ግን ተዋረድሁ ተናቅሁም።
16 መቅሠፍትህ በላዬ አለፈ፥ ግርማህም አስደነገጠኝ።
17 ሁልጊዜ እንደ ውኃ ከበቡኝ፥ በአንድነትም ያዙኝ።
18 ወዳጄንና ባልንጀራዬን ዘመዶቼንም ከመከራ የተነሣ ከእኔ አራቅህ።