መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 53
ለመዘምራን አለቃ በማኽላት፤ የዳዊት ትምህርት። ሰነፍ በልቡ። አምላክ የለም ይላል። ረከሱ በበደላቸውም ጐሰቈሉ፤ በጎ ነገርን የሚያደርጋት የለም።
2 የሚያስተውል እግዚአብሔርንም የሚፈልግ እንዳለ ያይ ዘንድ እግዚአብሔር ከሰማይ የሰው ልጆችን ተመለከተ።
3 ሁሉ በደሉ፥ አብረውም ረከሱ፤ አንድ ስንኳ በጎን ነገር የሚያደርጋት የለም።
4 ሕዝቤን እንጀራ እንደሚበላ የሚበሉ ግፍ አድራጊዎች ሁሉ አያውቁምን? እግዚአብሔርንም አይጠሩትም።
5 እግዚአብሔር የግብዞችን አጥንቶች በትኖአልና። በዚያ የሚያስፈራ ሳይኖር እጅግ ፈሩ፤ እግዚአብሔር ንቆአቸዋልና አሳፈርሃቸው።
6 መድኃኒትን ከጽዮን ለእስራኤል ማን በሰጠ! እግዚአብሔር የሕዝቡን ምርኮ በመለሰ ጊዜ፥ ያዕቆብ ደስ ይለዋል እስራኤልም ሐሤት ያደርጋል።