ምዕራፍ 28

የዳዊት መዝሙር።

አቤቱ፥ ወደ አንተ እጠራለሁ፤ ዝም ብትለኝ ወደ ጓድጓድ እንደሚወርዱት እንዳልመስል፥ አንተ አምላኬ፥ ዝም አትበለኝ።
2 ወደ መቅደስህ ማደሪያ እጄን ባነሣሁ ጊዜ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን የልመናዬን ቃል ስማ።
3 ከኃጥኣንና ከክፉ አድራጊዎች ጋር ነፍሴን አትውሰዳት፤ ክፋትም በልባቸው እያለ ከባልንጀራቸው ጋር ሰላም ከሚናገሩት ጋር አትጣለኝ።
4 እንደ ሥራቸው እንደ አካሄዳቸውም ክፉት ስጣቸው፤ እንደ እጃቸውም ሥራ ስጣቸው፤ ፍዳቸውን ወደ ራሳቸው መልስ።
5 ወደ እግዚአብሔር ሥራ ወደ እጆቹም አደራረግ አላሰቡምና ያፈርሳቸዋል እንጂ አይሠራቸውም።
6 የልመናዬን ቃል ሰምቶኛልና እግዚአብሔር ይመስገን።
7 እግዚአብሔር ኃይሌና ጋሻዬ ነው፤ ልቤ በእርሱ ታመነ እኔም ተረዳሁ፤ ሥጋዬም ደስ ይለዋል፥ ፈቅጄም አመሰግነዋለሁ።
8 እግዚአብሔር ለሕዝቡ ኃይላቸው ነው፥ ለቀባውም የመድኃኒቱ መታመኛ ነው።
9 ሕዝብህን አድን፥ ርስትህንም ባርክ፤ ጠብቃቸው፥ ለዘላለሙም ከፍ ከፍ አድርጋቸው።