ምዕራፍ 8

ለመዘምራን አለቃ በዋሽንት፤ የዳዊት መዝሙር።

አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ እጅግ ተመሰገነ፥ ምስጋናህ በሰማዮች ላይ ከፍ ከፍ ብሎአልና።
2 ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ ስለ ጠላትህ፥ ጠላትንና ቂመኛን ለማጥፋት።
3 የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችን ባየሁ ጊዜ፥ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን፥
4 ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጐበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?
5 ከመላእክት እጅግ ጥቂት አሳነስኸው፤ በክብርና በምስጋና ዘውድ ከለልኸው።
6 በእጆችህም ሥራ ሁሉ ላይ ሾምኸው፤ ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት፥
7 በጎችንም ላሞችንም ሁሉ ደግሞም የምድረ በዳውን እንስሶች፥
8 የሰማይንም ወፎች የባሕርንም ዓሦች፥ በባሕር መንገድ የሚሄደውንም ሁሉ።
9 አቤቱ ጌታችን፥ ስምህ በምድር ሁሉ እጅግ ተመሰገነ።