መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 77
ለመዘምራን አለቃ፤ ስለ ኤዶታም፤ የአሳፍ መዝሙር። በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፥ ቃሌም ወደ እግዚአብሔር ነው፥ እርሱም አደመጠኝ።
2 በመከራዬ ቀን እግዚአብሔርን ፈለግሁት፤ እጆቼ በሌሊት በፊቱ ናቸው፥ አላረፍሁምም፥ ነፍሴም መጽናናትን አልቻለችም።
3 እግዚአብሔርን አሰብሁት ደስ አለኝም፤ ተናገርሁ፥ ነፍሴም ፈዘዘች።
4 ዓይኖቼ እንዲተጉ ያዝሃቸው፤ ደነገጥሁ አልተናገርሁም።
5 የዱሮውን ዘመን አሰብሁ፤ የዘላለሙን ዓመታት አሰብሁ፤ አጠናጠንሁም
6 በሌሊት ከልቤ ጋር ተጫወትሁ፥ ነፍሴንም አነቃቃኋት።
7 እግዚአብሔር ለዘላለም ይጥላልን? እንግዲህስ ቸርነቱን አይጨምርምን?
8 ለዘላለምስ ምሕረቱ ለልጅ ልጅ ተቈረጠችን? የተናገረውስ ቃል አልቆአልን?
9 እግዚአብሔርስ ሞገሱን ረሳን? በቍጣውስ ምሕረቱን ዘጋውን?
10 ይህ ድካሜ ነው አልሁ፥ የልዑል ቀኝ እንደ ተለወጠ።
11 የእግዚአብሔርን ሥራ አስታወስሁ፤ የቀደመውን ተአምራትህን አስታወሳለሁና፤
12 በምግባርህም ሁሉ እናገራለሁ፥ በሥራህም እጫወታለሁ።
13 አቤቱ፥ መንገድህ በመቅደስ ውስጥ ነው፤ እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማን ነው?
14 ተኣምራትን የምታደርግ አምላክ አንተ ነህ። ለሕዝብህ ኃይልን አስታወቅሃቸው።
15 የያዕቆብንና የዮሴፍን ልጆች፥ ሕዝብህን በክንድህ አዳንሃቸው።
16 አቤቱ፥ ውኆች አዩህ፥ ውኆችም አይተውህ ፈሩ፤ ጥልቆች ተነዋወጡ፥ ውኆችም ጮኹ።
17 ደመኖች ድምፅን ሰጡ፥ ፍላጾችህም ወጡ።
18 የነጐድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነበረ፤ መብረቆች ለዓለም አበሩ፤ ምድር ተናወጠች ተንቀጠቀጠችም።
19 መንገድህ በባህር ውስጥ ነው፥ ፍለጋህም በብዙ ውኆች ነው፥ አረማመድህም አልታወቀም።
20 በሙሴና በአሮን እጅ ሕዝብህን እንደ በጎች መራሃቸው።