መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 94
በአራተኛ ሰንበት የዳዊት መዝሙር። እግዚአብሔር የበቀል አምላክ ነው። የበቀል አምላክ ተገለጠ።
2 የምድር ፈራጅ ሆይ፥ ከፍ ከፍ በል፤ ለትዕቢተኞች ፍዳቸውን ክፈላቸው።
3 አቤቱ፥ ኃጢአተኞች እስከ መቼ? ኃጢአተኞች እስከ መቼ ይጓደዳሉ?
4 ይከራከራሉ፥ ዓመፃንም ይናገራሉ፤ ዓመፃንም የሚያደርጉ ሁሉ ይናገራሉ።
5 አቤቱ፥ ሕዝብን አዋረዱ፥ ርስትህንም አስቸገሩ።
6 ባልቴቲቱንና ድሀ አደጉን ገደሉ፥ ስደተኛውንም ገደሉ።
7 እግዚአብሔር አያይም፥ የያዕቆብ አምላክ አያስተውልም አሉ።
8 የሕዝብ ደንቆሮች ሆይ፥ አስተውሉ፤ ሰነፎችማ መቼ ይጠበባሉ?
9 ጆሮን የተከለው አይሰማምን? ዓይንን የሠራው አያይምን?
10 አሕዛብንስ የሚገሥጸው፥ ለሰውም እውቀት የሚያስተምረው እርሱ አይዘልፍምን?
11 የሰዎች አሳብ ከንቱ እንደ ሆነ እግዚአብሔር ያውቃል።
12 -
13 ለኃጢአተኛ ጕድጓድ እስኪቈፈር ድረስ ከክፉዎች ዘመናት ይወገድ ዘንድ፥ አቤቱ፥ አንተ የገሠጽኸው ሕግህንም ያስተማርኸው ሰው ምስጉን ነው።
14 እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልምና፥ ርስቱንም አይተውምና
15 ፍርድ ወደ ጽድቅ እስኪመልስ ድረስ ልበ ቅኖችም ሁሉ ይከተሉአታል።
16 በክፉዎች ላይ ለእኔ የሚቆም ማን ነው? ዓመፃንስ በሚያደርጉ ላይ ለእኔ የሚከራከር ማን ነው?
17 እግዚአብሔር የረዳኝ ባይሆን ነፍሴ ለጥቂት ጊዜ በሲኦል ባደረች ነበር።
18 እግሮቼ ተሰናከሉ ባልሁ ጊዜ፥ አቤቱ፥ ምሕረትህ ረዳኝ።
19 አቤቱ፥ ለልቤ እንደ መከራዋ ብዛት ማጽናናትህ ነፍሴን ደስ አሰኛት።
20 በሕግ ላይ ዓመፅን የሚሠራ የዓመፅ ዙፋን ከአንተ ጋር አንድ ይሆናልን?
21 የጻድቅን ነፍስ ያደቡባታል፥ በንጹሕ ደምም ይፈርዳሉ።
22 እግዚአብሔር መጠጊያ ሆነኝ፥ አምላኬ የተስፋዬም ረዳት ነው።
23 እንደ በደላቸውም እንደ ክፋታቸውም ፍዳቸውን ይከፍላቸዋል፥ አምላካችን እግዚአብሔርም ያጠፋቸዋል።