ምዕራፍ 63

በኤዶምያስ ምድረ በዳ በነበረ ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር።

አምላኬ፥ አምላኬ፥ ወደ አንተ እገሠግሣለሁ፤ ነፍሴ አንተን ተጠማች፥ ሥጋዬ አንተን እንዴት ናፈቀች እንጨትና ውኃ በሌለበት በምድረ በዳ።
2 ኃይልህንና ክብርህን አይ ዘንድ እንዲሁ በመቅደስ ውስጥ ተመለከትሁህ።
3 ምሕረትህ ከሕይወት ይሻላልና ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል።
4 እንዲህ በሕይወቴ ዘመን አመሰግንሃለሁ፥ በአንተም ስም እጆቼን አነሣለሁ።
5 ነፍሴ በቅቤና በስብ እንደሚጠግቡ ትጠግባለች፥ ከንፈሮቼም ስምህን በደስታ ያመሰግናሉ።
6 በመኝታዬም አስብሃለሁ፥ በማለዳም እናገርልሃለሁ፤
7 ረዳቴ ሆነኸኛልና፥ በክንፎችህም ጥላ ደስ ይለኛልና።
8 ነፍሴ በኋላህ ተከታተለች፥ እኔንም ቀኝህ ተቀበለችኝ።
9 እነርሱ ግን ነፍሴን ለከንቱ ፈለጓት፤ ወደ ምድር ጥልቅ ይገባሉ።
10 ለሰይፍ እጅ አልፈው ይሰጣሉ፥ የቀበሮም እድል ፈንታ ይሆናሉ።
11 ንጉሥ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል፤ በእርሱ የሚምል ሁሉ ይከብራል፥ ሐሰትን የሚናገር አፍ ይዘጋልና።