ምዕራፍ 52

ለመዘምራን አለቃ፤ ኤዶማዊው ዶይቅ መጥቶ ለሳኦል። ዳዊት ወደ አቢሜሌክ ቤት መጥቶአል ብሎ በነገረው ጊዜ፤ የዳዊት ትምህርት።

ኃያል ሆይ፥ በክፋት ለምን ትጓደዳለህ? ሁልጊዜስ በመተላለፍ?
2 አንደበትህ ኃጢአትን ያስባል፤ እንደ ተሳለ ምላጭ ሽንገላን አደረግህ።
3 ከመልካም ይልቅ ክፋትን፥ ጽድቅንም ከመናገር ይልቅ ዓመፃን ወደድህ።
4 የሚያጠፉ ቃልን ሁሉ፥ የሽንገላ ምላስን ወደድህ።
5 ስለዚህ እግዚአብሔር ለዘላለም ያፈርስሃል፤ ከቤትህም ይነቅልሃል ያፈልስሃልም፥ ሥርህንም ከሕያዋን ምድር።
6 ጻድቃን አይተው ይፈራሉ፤ በእርሱም ይሥቃሉ እንዲህም ይላሉ።
7 እግዚአብሔርን ረዳቱ ያላደረገ፥ በባለጠግነቱም ብዛት የታመነ፥ በከንቱ ነገርም የበረታ ያ ሰው እነሆ።
8 እኔስ በእግዚአብሔር ቤት እንደ ለመለመ እንደ ወይራ ዛፍ ነኝ፤ ለዓለምና ለዘላለም በእግዚአብሔር ምሕረት ታመንሁ።
9 አድርገህልኛልና ለዘላለም አመሰግንሃለሁ፥ በቅዱሳንህም ዘንድ መልካም ነውና ስምህን ተስፋ አደርጋለሁ።