ምዕራፍ 137

በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን፤ ጽዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን።
2 በአኻያ ዛፎችዋ ላይ መሰንቆቻችንን ሰቀልን።
3 የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን፥ የወሰዱንም። የጽዮንን ዝማሬ ዘምሩልን አሉን።
4 የእግዚአብሔርን ዝማሬ በባዕድ ምድር እንዴት እንዘምራለን?
5 ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ብረሳሽ፥ ቀኜ ትርሳኝ።
6 ባላስብሽ፥ ምላሴ በጕሮሮዬ ይጣበቅ፤ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ።
7 አቤቱ፥ በኢየሩሳሌም ቀን የኤዶምን ልጆች አስብ። እስከ መሠረትዋ ድረስ አፍርሱ አፍርሱ ያሉአትን።
8 አንቺ ወራዳ የባቢሎን ልጅ ሆይ፥ ስለ ተበቀልሽን የሚበቀልሽ የተመሰገነ ነው።
9 ሕፃናቶችሽን ይዞ በዓለት ላይ የሚፈጠፍጣቸው የተመሰገነ ነው።