ምዕራፍ 126

የመዓርግ መዝሙር።

እግዚአብሔር የጽዮንን ምርኮ በመለሰ ጊዜ፥ እጅግ ደስተኞች ሆንን።
2 በዚያን ጊዜ አፋችን ደስታን፥ አንደበታችንም ሐሴትን ሞላ፤ በዚያን ጊዜ በአሕዛብ ዘንድ። እግዚአብሔር ታላቅ ነገርን አደረገላቸው ተባለ።
3 እግዚአብሔር ታላቅ ነገርን አደረገልን፥ ደስም አለን።
4 አቤቱ፥ በደቡብ እንዳሉ ፈሳሾች ምርኮአችንን መልስ።
5 በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ይለቅማሉ።
6 በሄዱ ጊዜ፥ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ።