ምዕራፍ 43

የዳዊት መዝሙር።

አቤቱ፥ ፍረድልኝ፥ ከጽድቅ ከራቁ ሕዝብም ክርክሬን ተከራከር፤ ከሸንጋይና ከግፈኛ ሰው አድነኝ።
2 አንተ አምላኬ ኃይሌም፥ ለምን ትተውኛለህ? ጠላቶቼ ሲያስጨንቁኝ ለምን አዝኜ እመላለሳለሁ?
3 ብርሃንህንና እውነትህን ላክ፤ እነርሱ ይምሩኝ፥ ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ።
4 ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ፥ ጕልማስነቴንም ደስ ወዳሰኛት ወደ አምላኬ እገባለሁ፤ አቤቱ አምላኬ፥ በበገና አመሰግንሃለሁ።
5 ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ።