መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 84
ለመዘምራን አለቃ፤ በዋሽንት፤ የቆሬ ልጆች መዝሙር። የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ ማደሪያዎችህ እንደምን የተወደዱ ናቸው!
2 ነፍሴ የእግዚአብሔርን አደባባዮች ትወድዳለች ትናፍቅማለች፤ ልቤም ሥጋዬም በሕያው አምላክ ደስ ተሰኘ።
3 ወፍ ለእርስዋ ቤትን አገኘች፥ ዋኖስም ጫጩቶችዋን የምታኖርበት ቤት አገኘች፤ የሠራዊት አምላክ ንጉሤም አምላኬም ሆይ፥ እርሱ መሠዊያህ ነው።
4 በቤትህ የሚኖሩ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው፤ ለዓለምና ለዘላለምም ያመሰግኑሃል።
5 አቤቱ፥ እርዳታው ከአንተ ዘንድ የሆነለት፥ በልቡም የላይኛውን መንገድ የሚያስብ ሰው ምስጉን ነው።
6 በልቅሶ ሸለቆ ውስጥ በወሰነው ስፍራ የሕግ መምህር በረከትን ይሰጣልና።
7 ከኃይል ወደ ኃይል ይሄዳሉ፤ የአማልክት አምላክ በጽዮን ይታያል።
8 የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፤ የያዕቆብ አምላክ ሆይ፥ አድምጥ።
9 አቤቱ፥ መታመናችንን እይልን፥ ወደ ቀባኸውም ፊት ተመልከት።
10 ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች፤ በኃጥኣን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፥ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ።
11 እግዚአብሔር አምላክ ምሕረትንና እውነትን ስለ ወደደ፥ ሞገስንና ክብርን ይሰጣል፤ እግዚአብሔር በቅንነት የሚሄዱትን ከመልካም ነገር አያሳጣቸውም።
12 የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ በአንተ የታመነ ሰው ምስጉን ነው።