ምዕራፍ 121

የመዓርግ መዝሙር።

ዓይኖቼ ወደ ተራሮች አነሣሁ፤ ረዳቴ ከወዴት ይምጣ?
2 ረዳቴ ሰማይና ምድርን ከሠራ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።
3 እግርህን ለመናወጥ አይሰጠውም፤ የሚጠብቅህም አይተኛም።
4 እነሆ፥ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም።
5 እግዚአብሔር ይጠብቅሃል፥ እግዚአብሔርም በቀኝ እጅህ በኩል ይጋርድሃል።
6 ፀሐይ በቀን አያቃጥልህም ጨረቃም በሌሊት።
7 እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፥ ነፍስህንም ይጠብቃታል።
8 ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም እግዚአብሔር መውጣትህና መግባትህን ይጠብቃል።