መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 95
የዳዊት ምስጋና መዝሙር። ኑ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበለን፤ ለአምላክ ለመድኃኒታችን እልል እንበል።
2  በምስጋና ወደ ፊቱ እንድረስ፥ በዝማሬም ለእርሱ እልል እንበል፤
3  እግዚአብሔር ታላቅ አምላክ ነውና፥ በአማልክትም ሁሉ ላይ ታላቅ ንጉሥ ነውና።
4  እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥላቸውም፤ የምድር ዳርቻዎችም በእጁ ውስጥ ናቸው፥ የተራሮች ከፍታዎች የእርሱ ናቸው።
5  ባሕር የእርሱ ናት እርሱም አደረጋት፥ የብስንም እጆቹ ሠሩአት።
6  ኑ፥ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ፤ በእርሱ ባደረገን በእግዚአብሔር ፊት እንበርከክ፤
7  እርሱ አምላካችን ነውና፥ እኛ የማሰማርያው ሕዝብ የእጁም በጎች ነንና።
8  በምድረ በዳ እንደ ተፈታተኑት እንዳስቈጡት ጊዜ፥ ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ ልባችሁን አታጽኑ።
9  የተፈታተኑኝ አባቶቻችሁ ፈተኑኝ ሥራዬንም አዩ።
10  ያችን ትውልድ አርባ ዓመት ተቈጥቻት ነበር። ሁልጊዜ ልባቸው ይስታል፥ እነርሱም መንገዴን አላወቁም አልሁ።
11  ወደ ዕረፍቴም እንዳይገቡ በቁጣዬ ማልሁ።