መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 60
ለመዘምራን አለቃ፤ የሶርያን ሁለቱን ወንዞችና የሶርያን ሶባልን ባቃጠለ ጊዜ ኢዮአብም ተመልሶ ከኤዶማውያን ሰዎች በጨው ሸለቆ አሥራ ሁለት ሺህ በገደለ ጊዜ ለትምህርት የዳዊት ቅኔ። አቤቱ፥ ጣልኸን አፈረስኸንም፤ ተቈጣኸን ይቅርም አልኸን።
2 ምድርን አናወጥሃት አወክሃትም፤ ተናውጣለችና ቍስልዋን ፈውስ።
3 ለሕዝብህ ጭንቅን አሳየሃቸው፥ አስደንጋጩንም ወይን አጠጣኸን።
4 ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፥ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው።
5 ወዳጆችህ እንዲድኑ በቀኝህ አድን፥ አድምጠኝም።
6 እግዚአብሔር በቅድስናው ተናገረ፤ ደስ ይለኛል፥ ሴኬምንም እካፈላለሁ፥ የሱኮትንም ሸለቆ እሰፍራለሁ።
7 ገለዓድ የእኔ ነው፥ ምናሴም የእኔ ነው፤ ኤፍሬም የራሴ መጠጊያ ነው። ይሁዳ ንጉሤ ነው፤
8 ሞዓብ መታጠቢያዬ ነው፥ በኤዶምያስ ላይ ጫማዬን እዘረጋለሁ፤ ፍልስጥኤም ይገዙልኛል።
9 ወደ ጽኑ ከተማ ማን ይወስደኛል? ማንስ እስከ ኤዶምያስ ይመራኛል?
10 አቤቱ፥ የጣልኸን አንተ አይደለህምን? አምላክ ሆይ፥ ከሠራዊታችን ጋር አትወጣም።
11 በመከራችን ረድኤትን ስጠን የሰውም ማዳን ከንቱ ነው።
12 በእግዚአብሔር ኃይልን እናደርጋለን እርሱ የሚያስጨንቁንን ያዋርዳቸዋልና።