መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 111
 ሃሌ ሉያ። አቤቱ፥ በቅኖች ሸንጎ በጉባኤም በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ።
2  የእግዚአብሔር ሥራ ታላቅ ናት፥ ደስ በሚሰኙባት ሁሉ ዘንድ የተፈለገች ናት።
3  ሥራው ምስጋናና ግርማ ነው፤ ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል።
4  ለተአምራቱ መታሰቢያን አደረገ፤ እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው።
5  ለሚፈሩት ምግብን ሰጣቸው፤ ኪዳኑንም ለዘላለም ያስባል።
6  የአሕዛብን ርስት ይሰጣቸው ዘንድ ለሕዝቡ የሥራውን ብርታት አሳየ።
7  የእጆቹ ሥራ እውነትና ፍርድ ነው፤ ትእዛዙም ሁሉ የታመነ ነው፥
8  ለዘላለምም የጸና ነው፥ በእውነትና በቅንም የተሠራ ነው።
9  መድኃኒትንም ለሕዝቡ ሰደደ፥ ኪዳኑንም ለዘላለም አዘዘ፤ ስሙ የተቀደሰና የተፈራ ነው።
10  የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፥ ለሚያደርጓትም ሁሉ ደኅና ማስተዋል አላቸው፤ ምስጋናውም ለዘላለም ይኖራል።