መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 80
ለመዘምራን አለቃ፤ በመለከቶች፤ ስለ አሦራውያን፤ የአሳፍ የምስክር መዝሙር። ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ፥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ፥ አድምጥ፤ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፥ ተገለጥ።
2 በኤፍሬምና በብንያም በምናሴም፤ ኃይልህን አንሣ እኛንም ለማዳን ና።
3 አቤቱ፥ መልሰን፥ ፊትህንም አብራ፥ እኛም እንድናለን።
4 የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ በባሪያህ ጸሎት ላይ እስከ መቼ ትቈጣለህ?
5 የእንባ እንጀራን ትመግበናለህ፥ እንባም በስፍር ታጠጣናለህ።
6 ለጎረቤቶቻችን ክርክር አደረግኸን፥ ጠላቶቻችንም በላያችን ተሣለቁብን።
7 የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ መልሰን፥ ፊትህንም አብራ፥ እኛም እንድናለን።
8 ከግብጽ የወይን ግንድ አመጣህ፤ አሕዛብን አባረርህ እርስዋንም ተከልህ።
9 በፊትዋም ስፍራን አዘጋጀህ፥ ሥሮችዋንም ተከልህ ምድርንም ሞላች።
10 ጥላዋ ተራሮችን ከደነ፥ ጫፎችዋም እንደ እግዚአብሔር ዝግባ ሆኑ።
11 ቅርንጫፎችዋንም እስከ ባሕር፥ ቡቃያዋንም እስከ ወንዙ ዘረጋች።
12 አጥርዋን ለምን አፈረስህ? መንገድ አላፊም ሁሉ ይቀጥፋታል።
13 የዱር እርያ አረከሳት፥ የአገር አውሬም ተሰማራባት።
14 የሠራዊት አምላክ ሆይ፥ እንግዲህ ተመለስ፤ ከሰማይ ተመልከት፥ እይም፥ ይህችንም የወይን ግንድ ጐብኝ።
15 በሰው ልጅ ለአንተ ያጸናኸውን ቀኝህ የተከላትን አንሣ።
16 በእሳት ተቃጥላለች ተነቅላማለች፤ ከፊትህ ተግሣጽም የተነሣ ይጠፋሉ።
17 ለአንተ ባጸናኸው በሰው ልጅ ላይ፥ በቀኝህ ሰው ላይ እጅህ ትሁን።
18 ከአንተም አንራቅ፤ አድነን ስምህንም እንጠራለን።
19 የሠራዊት አምላክ አቤቱ፥ መልሰን፥ ፊትህንም አብራ፥ እኛም እንድናለን።