ምዕራፍ 143

ልጁ ባሳደደው ጊዜ፤ የዳዊት መዝሙር።

አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማ፤ በእውነትህ ልመናዬን አድምጥ፥ በጽድቅህም መልስልኝ።
2 ሕያው ሁሉ በፊትህ ጻድቅ አይደለምና ከባሪያህ ጋር ወደ ፍርድ አትግባ።
3 ጠላትህ ነፍሴን አሳድዶአታል፥ ሕይወቴንም በምድር ውስጥ አጐስቍሎአታል፤ ቀድሞ እንደ ሞተ ሰው በጨለማ አኑሮኛል።
4 ነፍሴ በውስጤ አለቀችብኝ፥ ልቤም በውስጤ ደነገጠብኝ።
5 የቀድሞውን ዘመን አሰብሁ፥ ሥራህንም ሁሉ አሰላሰልሁ፤ የእጅህንም ሥራ ተመለከትሁ።
6 እጆቼን ወደ አንተ ዘረጋሁ፤ ነፍሴም እንደ ምድረ በዳ አንተን ተጠማች።
7 አቤቱ፥ ፈጥነህ ስማኝ፤ ነፍሴ አልቃለች፤ ፊትህን ከኔ አትመልስ፥ ወደ ጕድጓድም እንደሚወርዱ አልሁን።
8 አንተን ታምኛለሁና በማለዳ ምሕረትህን አሰማኝ፤ አቤቱ፥ ነፍሴን ወደ አንተ አንሥቻለሁና የምሄድበትን መንገድ አስታውቀኝ።
9 አቤቱ፥ ወደ አንተ ተማፅኛለሁና ከጠላቶቼ አድነኝ።
10 አንተ አምላኬ ነህና ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ፤ ቅዱስ መንፈስህም በጽድቅ ምድር ይምራኝ።
11 አቤቱ፥ ስለ ስምህ ሕያው አድርገኝ፤ በጽድቅህም ነፍሴን ከመከራዋ አውጣት።
12 በምሕረትህ ጠላቶቼን ደምስሳቸው፥ እኔ ባሪያህ ነኝና ነፍሴን የሚያስጨንቁአትን ሁሉ አጥፋቸው።