መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 86
የዳዊት ጸሎት። አቤቱ፥ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል አድምጠኝም፥ ችግረኛና ምስኪን ነኝና።
2 ቅዱስ ነኝና ነፍሴን ጠብቅ፤ አምላኬ ሆይ፥ አንተን የታመነውን ባሪያህን አድነው።
3 አቤቱ፥ ቀኑን ሁሉ ወደ አንተ እጮኻለሁና ማረኝ።
4 የባሪያህን ነፍስ ደስ አሰኛት፥ አቤቱ፥ ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁና።
5 አቤቱ፥ አንተ መሓሪና ይቅር ባይ ነህና፥ ምሕረትህም ለሚጠሩህ ሁሉ ብዙ ነውና።
6 አቤቱ፥ ጸሎቴን አድምጥ፥ የልመናዬንም ድምፅ ስማ።
7 ትመልስልኛለህና በመከራዬ ቀን ወደ አንተ እጠራለሁ።
8 አቤቱ፥ ከአማልክት የሚመስልህ የለም፥ እንደ ሥራህም ያለ የለም።
9 ያደረግሃቸው አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ፥ አቤቱ፥ በፊትህም ይሰግዳሉ፥ ስምህንም ያከብራሉ፤
10 አቤቱ፥ ድንቅ የምታደርግ አንተ ታላቅ ነህና፥ አንተም ብቻህን ታላቅ አምላክ ነህና።
11 አቤቱ፥ መንገድህን ምራኝ፥ በእውነትህም እሄዳለሁ፤ ስምህን ለመፍራት ልቤ ደስ ይለዋል።
12 አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፥ ለዘላለምም ስምህን አከብራለሁ፤
13 ምሕረትህ በእኔ ላይ ታላቅ ናትና፥ ነፍሴንም ከታችኛይቱ ሲኦል አድነሃታልና።
14 አቤቱ፥ ዓመፀኞች በእኔ ላይ ተነሥተዋል፥ የክፉዎችንም ማኅበር ነፍሴን ፈለጉአት፤ በፊታቸውም አላደረጉህም።
15 አቤቱ፥ አንተ ግን መሓሪና ርኅሩኅ አምላክ ነህ፤ መዓትህ የራቀ ምሕረትህም እውነትህም የበዛ፤
16 ወደ እኔ ተመልከት ማረኝም፤ ለባሪያህ ኃይልህን ስጥ፥ የሴት ባሪያህንም ልጅ አድን።
17 ምልክትንም ለመልካም ከእኔ ጋር አድርግ፤ የሚጠሉኝ ይዩ ይፈሩም፥ አቤቱ፥ አንተ ረድተኸኛልና፥ አጽንተኸኛልምና።