ምዕራፍ 8

እግዚአብሔርም። ታላቅ ሰሌዳ ወስደህ። ምርኮ ፈጠነ፥ ብዝበዛ ቸኰለ ብለህ በሰው ፊደል ጻፍበት።
2 ፤ የታመኑትን ሰዎች ካህኑን ኦርዮንና የበራክዩን ልጅ ዘካርያስን ምስክሮች አድርግልኝ አለኝ።
3 ፤ ወደ ነቢይቱም ቀረብሁ፤ እርስዋም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች።
4 ፤ እግዚአብሔርም። ሕፃኑ አባቱንና እናቱን መጥራት ሳያውቅ የደማስቆን ሀብትና የሰማርያን ምርኮ በአሦር ንጉሥ ፊት ይወስዳልና ስሙን። ምርኮ ፈጠነ፥ ብዝበዛ ቸኰለ ብለህ ጥራው አለኝ።
5 ፤ እግዚአብሔርም ደግሞ ተናገረኝ እንዲህም አለኝ።
6 ፤ ይህ ሕዝብ በቀስታ የሚሄደውን የሰሊሆምን ውኃ ጠልቶአልና፥ ረአሶንንና የሮሜልዩንም ልጅ ወዶአልና ስለዚህ፥
7 ፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር ብርቱና ብዙ የሆነውን የወንዝ ውኃ፥ የአሦርን ንጉሥና ክብሩን ሁሉ፥ ያመጣባቸዋል፤ መስኖውንም ሁሉ ሞልቶ ይወጣል፥ በዳሩም ሁሉ ላይ ይፈስሳል፤
8 ፤ እየጐረፈም ወደ ይሁዳ ይገባል፤ እያጥለቀለቀም ያልፋል፥ እስከ አንገትም ይደርሳል፤ አማኑኤል ሆይ፥ የክንፉ መዘርጋት የአገርህን ስፋት ትሞላለች።
9 ፤ አሕዛብ ሆይ፥ እወቁና ደንግጡ፤ እናንተም ምድራችሁ የራቀ ሁሉ፥ አድምጡ፤ ታጠቁም፥ ደንግጡ፤ ታጠቁ፤ ደንግጡ።
10 ፤ ተመካከሩ፥ ምክራችሁም ይፈታል፤ ቃሉን ተናገሩ፥ ቃሉም አይጸናም፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና።
11 ፤ እግዚአብሔርም በጽኑ እጅ እንዲህ ተናገረኝ፥ በዚህም ሕዝብ መንገድ አንዳልሄድ አስጠነቀቀኝ፥ እንዲህም አለኝ።
12 ፤ ይህ ሕዝብ። ዱለት ነው በሚሉት ሁሉ። ዱለት ነው አትበሉ፤ መፈራታቸውንም አትፍሩ፥ አትደንግጡ።
13 ፤ ነገር ግን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርን ቀድሱት፤ የሚያስፈራችሁና የሚያስደነግጣችሁም እርሱ ይሁን።
14 ፤ እርሱም ለመቅደስ ይሆናል፤ ነገር ግን ለሁለቱ ለእስራኤል ቤቶች ለዕንቅፋት ድንጋይና ለማሰናከያ ዓለት፥ በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ለወጥመድና ለአሽክላ ይሆናል።
15 ፤ ብዙዎችም በእርሱ ይሰናከላሉ፥ ይወድቁማል፥ ይሰበሩማል፥ ይጠመዱማል፥ ይያዙማል።
16 ፤ ምስክሩን እሰር፤ በደቀ መዛሙርቶቼም መካከል ሕጉን አትም።
17 ፤ ከያዕቆብም ቤት ፊቱን የመለሰውን እግዚአብሔርን እጠብቃለሁ፥ እተማመንበትማለሁ።
18 ፤ እነሆ፥ እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ለእስራኤል በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክትና ተአምራት ነን።
19 ፤ እነርሱም። የሚጮኹትንና ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው የሚናገሩትን መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ጠይቁ ባሉአችሁ ጊዜ፥ ሕዝቡ ከአምላኩ መጠየቅ አይገባውምን? ወይስ ለሕያዋን ሲሉ ሙታንን ይጠይቃሉን?
20 ፤ ወደ ሕግና ወደ ምስክር ሂዱ! እንዲህም ያለውን ቃል ባይናገሩ ንጋት አይበራላቸውም።
21 ፤ እነርሱም ተጨንቀውና ተርበው ያልፋሉ፤ በተራቡም ጊዜ ተቈጥተው ንጉሣቸውንና አምላካቸውን ይረግማሉ፥ ወደ ላይም ይመለከታሉ፤
22 ፤ ወደ ምድርም ይመለከታሉ፥ እነሆም፥ መከራና ጨለማ የሚያስጨንቅም ጭጋግ አለ፤ ወደ ድቅድቅም ጨለማ ይሰደዳሉ።