ምዕራፍ 36

እንዲህም ሆነ፤ በንጉሡ በሕዝቅያስ በአሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ይሁዳ ወደ ተመሸጉት ከተሞች ሁሉ ወጥቶ ወሰዳቸው።
2 ፤ የአሦርም ንጉሥ ራፋስቂስን ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም ላከ፥ እርሱም በአጣቢው እርሻ መንገድ ባለችው በላይኛይቱ ኵሬ መስኖ አጠገብ ቆመ።
3 ፤ የቤቱም አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እርሱ ወጡ።
4 ፤ ራፋስቂስም አላቸው። ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት። ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል። ይህ የምትታመንበት መተማመኛ ምንድር ነው?
5 ፤ እኔ። ለሰልፍ የሆነው ምክርህና ኃያልህ ከንቱ ነገር ነው አልሁ፤ አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው?
6 ፤ እነሆ፥ በዚህ በተቀጠቀጠ በሸምበቆ በትር በግብጽ ትታመናለህ፤ ሰው ቢመረኰዘው ተሰብሮ በእጁ ይገባል ያቈስለውማል የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ አንዲሁ ነው።
7 ፤ አንተም። በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን ብትለኝ፥ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን። በዚህ መሠዊያ ፊት ስገዱ ብሎ የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያዎቹን ይስፈረሰ ይህ አይደለምን?
8 ፤ አሁን እንግዲህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተወራረድ፥ የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ማግኘት ቢቻልህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ።
9 ፤ ስለ ሰረገሎችና ስለ ፈረሶኞች በግብጽ ስትታመን፥ ከጌታዬ ባሪያዎች የሚያንሰውን የአንዱን አለቃ ፊት ትቃወም ዘንድ እንዴት ይቻልሃል?
10 ፤ አሁንም በውኑ ያለ እግዚአብሔር ትእዛዝ ይህን አገር አጠፋ ዘንድ ወጥቻለሁን? እግዚአብሔር። ወደዚህ አገር ወጥተህ አጥፋው አለኝ።
11 ፤ ኤልያቄምና ሳምናስ ዮአስም ራፋስቂስን። እኛ እንሰማለንና እባክህ፥ በሶርያ ቋንቋ ለባሪያዎችህ ተናገር፤ በቅጥርም ላይ ባለው ሕዝብ ጆሮ በአይሁድ ቋንቋ አትናገረን አሉት።
12 ፤ ራፋስቂስ ግን። ጌታዬ ይህን ቃል እናገር ዘንድ ወደ አንተና ወደ ጌታህ ልኮኛልን? ከእናንተ ጋር ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥር ላይ ወደ ተቀመጡት ሰዎች አይደለምን? አላቸው።
13 ፤ ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በአይሁድ ቋንቋ እንዲህ ብሎ ጮኸ። የታላቁን የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ።
14 ፤ ንጉሡ እንዲህ ይላል። ያድናችሁ ዘንድ አይችልምና ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤
15 ፤ ሕዝቅያስም። እግዚአብሔር በእርግጥ ያድነናል ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ።
16 ፤ ሕዝቅያስንም አትስሙ፤ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል። ከእኔ ጋር ታረቁ ወደ እኔም ውጡ፤ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ብሉ፥ ከጕድጓዳችሁም ውኃ ጠጡ፤
17 ፤ ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፥ እህልና የወይን ጠጅ፥ እንጀራና ወይን ወዳለበት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ ነው።
18 ፤ ሕዝቅያስም። እግዚአብሔር ያድነናል ብሎ እንዳያታልላችሁ ተጠንቀቁ። በውኑ የአሕዛብ አማልክት አገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋልን?
19 ፤ የሐማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፈርዋይም አማልክት ወዴት አሉ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን?
20 ፤ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድን ዘንድ ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ አገሩን ከእጄ ያዳነ ማን ነው?
21 ፤ እነርሱም ዝም አሉ፥ አንዳችም አልመለሱለትም፤ ንጉሡ አንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና።
22 ፤ የቤቱ አዛዥ የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም ጸሐፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሐፊም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፥ የራፋስቂስንም ቃል ነገሩት።