ትንቢተ ኢሳይያስ
ምዕራፍ 57
ጻድቅ ይሞታል፥ በልቡም ነገሩን የሚያኖር የለም፤ ምሕረተኞችም ይወገዳሉ፥ ጽድቅም ከክፋት ፊት እንደ ተወገደ ማንም አያስተውልም።
2 ፤ ወደ ሰላም ይገባል፤ በቅንነት የሄደ በአልጋው ላይ ያርፋል።
3 ፤ እናንተ የአስማተኛይቱ ልጆች፥ የአመንዝራውና የጋለሞታይቱ ዘር፥ ወደዚህ ቅረቡ።
4 ፤ በማን ታላግጣላችሁ? በማንስ ላይ አፋችሁን ታላቅቃላችሁ? ምላሳችሁንስ በማን ላይ ታስረዝማላችሁ?
5 ፤ እናንተ በአድባር ዛፎች መካከል በለመለመም ዛፍ ሁሉ በታች በፍትወት የምትቃጠሉ፥ እናንተም በሸለቆች ውስጥ በዓለትም ስንጣቂዎች በታች ሕፃናትን የምታርዱ፥ የዓመፅ ልጆችና የሐሰት ዘር አይደላችሁምን?
6 ፤ በሸለቆው ውስጥ ያሉ የለዘቡ ድንጋዮች እድል ፈንታሽ ናቸው፥ እነርሱም ዕጣሽ ናቸው፤ ለእነርሱም የመጠጥ ቍርባን አፍስሰሻል፥ የእህልንም ቍርባን አቅርበሻል። እንግዲህ በዚህ ነገር አልቈጣምን?
7 ፤ ከፍ ባለውም በረዘመውም ተራራ ላይ መኝታሽን አደረግሽ፥ መሥዋዕትንም ትሠዊ ዘንድ ወደዚያ ወጣሽ።
8 ፤ ከመዝጊያውና ከመቃኑ በኋላ መታሰቢያሽን አደረግሽ፤ እኔን ትተሽ ለሌላ ተገልጠሻል፥ ወጥተሽ መኝታሽን አስፍተሻል፤ ቃል ኪዳንም ተጋባሻቸው፥ ባየሽበትም ስፍራ ሁሉ መኝታቸውን ወደድሽ።
9 ፤ ዘይትም ይዘሽ ወደ ንጉሡ ሄድሽ፥ ሽቱሽንም አበዛሽ፥ መልእክተኞችሽንም ወደ ሩቅ ላክሽ፥ እስከ ሲኦልም ድረስ ተዋረድሽ።
10 ፤ በመንገድሽም ብዛት ደከምሽ፥ ነገር ግን። ተስፋ የለም አላልሽም፤ የጕልበትን መታደስ አገኘሽ፥ ስለዚህም አልዛልሽም።
11 ፤ ሐሰትን የተናገርሺው እኔንም ያላሰብሺው በልብሽም ነገሩን ያላኖርሺው ማንን ሰግተሽ ነው? ማንንስ ፈርተሽ ነው? እኔ ብዙ ጊዜ ዝም አልሁ፥ አንቺም አልፈራሽም።
12 ፤ እኔ ጽድቅሽን እናገራለሁ፥ ሥራሽም አይረባሽም።
13 ፤ ወደ አንቺ የሰበሰብሻቸው በጮኽሽ ጊዜ ይታደጉሽ፤ ንፋስ ግን ይወስዳቸዋል ሽውሽውታም ሁሉን ያስወግዳቸዋል። በእኔ የታመነ ግን ምድሪቱን ይገዛል፥ የተቀደሰውንም ተራራዬን ይወርሳል።
14 ፤ እርሱም። ጥረጉ፥ መንገድን አዘጋጁ፥ ከሕዝቤም መንገድ ዕንቅፋትን አውጡ ይላል።
15 ፤ ለዘላለም የሚኖር ስሙም ቅዱስ የሆነ፥ ከፍ ያለው ልዑል እንዲህ ይላል። የተዋረዱትን ሰዎች መንፈስ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠውንም ልብ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠና የተዋረደ መንፈስ ካለው ጋር በከፍታና በተቀደሰ ስፍራ እቀመጣለሁ።
16 ፤ መንፈስም የፈጠርሁትም ነፍስ ከፊቴ እንዳይዝል ለዘላለም አልጣላም፥ ሁልጊዜም አልቈጣም።
17 ፤ ስለ ኃጢአቱ ጥቂት ጊዜ ተቈጥቼ ቀሠፍሁት፥ ፊቴን ሰውሬ ተቈጣሁ፤ እርሱም በልቡ መንገድ እያፈገፈገ ሄደ።
18 ፤ መንገዱን አይቻለሁ እፈውሰውማለሁ፥ እመራውማለሁ፥ ለእርሱና ስለ እርሱም ለሚያለቅሱ መጽናናትን እመልሳለሁ።
19 ፤ የከንፈሮችን ፍሬ እፈጥራለሁ፤ በሩቅም በቅርብም ላለው ሰላም ሰላም ይሁን፥ እፈውሰውማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
20 ፤ ክፉዎች ግን እንደሚንቀሳቀስ ባሕር ናቸው፤ ጸጥ ይል ዘንድ አይችልምና፥ ውኆቹም ጭቃና ጕድፍ ያወጣሉና።
21 ፤ ለክፉዎች ሰላም የላቸውም ይላል አምላኬ።