ምዕራፍ 28

ለኤፍሬም ሰካሮች ትዕቢት አክሊል፥ በወይን ጠጅ ለተሸነፉ በወፍራም ሸለቆአቸው ራስ ላይ ላለችም ለረገፈች ለክብሩ ጌጥ አበባ ወዮ!
2 ፤ እነሆ፥ በጌታ ዘንድ ኃያል ብርቱ የሆነ አለ። እንደ በረዶ ወጨፎ፥ እንደሚያጠፋም ዐውሎ ነፋስ፥ እንደሚያጥለቀልቅም እንደ ታላቅ ውኃ ፈሳሽ በጠነከረ እጅ ወደ ምድር ይጥላል።
3 ፤ የኤፍሬም ሰካሮች ትዕቢት አክሊል በእግር ይረገጣል፤
4 ፤ በወፍራሙ ሸለቆ ራስ ላይ ያለች የረገፈች የክብሩ ጌጥ አበባ ከመከር በፊት አስቀድማ እንደምትበስል በለስ ትሆናለች፤ ሰው ባያት ጊዜ በእጁ እንዳለች ይበላታል።
5 ፤ በዚያ ቀን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለቀሩት ሕዝቡ የክብር ዘውድና የጌጥ አክሊል ይሆናል፤
6 ፤ በፍርድ ወንበር ላይ ለሚቀመጥም የፍርድ መንፈስ፥ ሰልፉን ወደ በር ለሚመልሱም ኃይል ይሆናል።
7 ፤ እነዚህም ደግሞ ከወይን ጠጅ የተነሣ ይስታሉ፥ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይፋንናሉ፤ ካህኑና ነቢዩ ከሚያሰክር መጠጥ የተነሣ ይስታሉ፥ በወይን ጠጅም ይዋጣሉ፥ ከሚያሰክርም መጠጥ የተነሣ ይፋንናሉ፤ በራእይ ይስታሉ፥ በፍርድም ይሰናከላሉ።
8 ፤ ማዕዱ ሁሉ ትፋትንና ርኵሰትን ተሞልቶአታል፤ ንጹሕ ስፍራ እንኳ የለም።
9 ፤ እውቀትን ለማን ያስተምረዋል? ወይስ ወሬ ማስተዋልን ለማን ይሰጣል? ወተትን ለተዉ ወይስ ጡትን ለጣሉ ነውን?
10 ፤ ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ነው።
11 ፤ በባዕድ አፍ በልዩም ልሳን ለዚህ ሕዝብ ይናገራል፤ እርሱም። ዕረፍት ይህች ናት፥
12 ፤ የደከመውን አሳርፉ፤ ይህችም ማረፊያ ናት አላቸው፤ እነርሱ ግን መስማትን እንቢ አሉ።
13 ፤ ስለዚህ ሄደው ወደ ኋላ እንዲወድቁ እንዲሰበሩም ተጠምደውም እንዲያዙ የእግዚአብሔር ቃል ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ይሆንላቸዋል።
14 ፤ ስለዚህ በኢየሩሳሌም ያለውን ሕዝብ የምትገዙ ፌዘኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።
15 ፤ እናንተም። ከሞት ጋር ቃል ኪዳን አድርገናል፥ ከሲኦልም ጋር ተማምለናል፤ ሐሰትን መሸሸጊያችን አድርገናልና፥ በሐሰትም ተሰውረናልና የሚትረፈረፍ መቅሠፍት ባለፈ ጊዜ አይደርስብንም ስላላችሁ፥
16 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በጽዮን ድንጋይን ለመሠረት አስቀምጣለሁ፤ የተፈተነውን፥ የከበረውን፥ መሠረቱ የጸናውን የማዕዘን ድንጋይ፤ የሚያምን አያፍርም።
17 ፤ ለገመድ ፍርድን ለቱንቢም ጽድቅን አደርጋለሁ፤ በረዶውም የሐሰትን መሸሸጊያ ይጠርጋል፥ ውኆችም መሰወሪያውን ያሰጥማሉ።
18 ፤ ከሞትም ጋር ያደረጋችሁት ቃል ኪዳን ይፈርሳል፥ ከሲኦልም ጋር የተማማላችሁት መሐላ አይጸናም፤ የሚትረፈረፍ መቅሠፍት ባለፈ ጊዜ ትረገጡበታላችሁ።
19 ፤ ባለፈም ጊዜ ይወስዳችኋል፤ ማለዳ ማለዳ ቀንና ሌሊት ያልፋል፤ ወሬውንም ማስተዋል ድንጋጤ ይሆናል።
20 ፤ ሰው በእርሱ ላይ ተዘርግቶ ቢተኛ አልጋው አጭር ነው፤ ሰውም ሰውነቱን መሸፈን ቢወድድ መጐናጸፊያ ጠባብ ነው።
21 ፤ እግዚአብሔርም ሥራውን ማለት እንግዳ ሥራውን ይሠራ ዘንድ፥ አድራጎቱንም ማለት ያልታወቀውን አድራጎቱን ያደርግ ዘንድ በፐራሲም ተራራ እንደ ነበረ ይነሣል፥ በገባዖንም ሸለቆ እንደ ነበረ ይቈጣል።
22 ፤ አሁንም በምድር ሁሉ ላይ የሚጸናውን የጥፋት ትእዛዝ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ሰምቻለሁና እስራት እንዳይጸንባችሁ አታፊዙ።
23 ፤ አድምጡ ድምፄንም ስሙ፤ ልብ አድርጉ ንግግሬንም ስሙ።
24 ፤ በውኑ ገበሬ ሊዘራ ሁልጊዜ ያርሳልን? ወይስ ሁልጊዜ እርሻውን ይገለግላልን?
25 ፤ ጓሉንስ ይከሰክሳልን? እርሻውን ባስተካከለ ጊዜ ጥቁሩን አዝሙድ፥ ከሙኑንም፥ ስንዴውንም በተርታ፥ ገብሱንም በስፍራው፥ አጃንም በደረጃው የሚዘራ አይደለምን?
26 ፤ ይህንም ብልሃት አምላኩ ያስታውቀዋል ያስተምረውማል።
27 ፤ ጥቁሩ አዝሙድ በተሳለች መሄጃ አያኬድም፥ የሰረገላም መንኰራኵር በከሙን ላይ አይዞርም፤ ነገር ግን ጥቁሩ አዝሙድ በሽመል ከሙኑም በበትር ይወቃል።
28 ፤ የእንጀራ እህል ይደቅቃልን? ለዘላለም አያኬደውም፤ የሰረገላውን መንኰራኵርና ፈረሶቹን ምንም ቢያስኬድበት አያደቅቀውም።
29 ፤ ይህም ደግሞ ድንቅ ምክር ከሚመክር በግብሩም ማለፊያ ከሆነው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ወጥቶአል።