ምዕራፍ 19

ስለ ግብጽ የተነገረ ሸክም። እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና እይበረረ ወደ ግብጽ ይመጣል፤ የግብጽም ጣዖታት በፊቱ ይርዳሉ፥ የግብጽም ልብ በውስጥዋ ይቀልጣል።
2 ፤ ግብጻውያንን በግብጻውያን ላይ አስነሣለሁ፤ ወንድምም ወንድሙን፥ ሰውም ባልንጀራውን፥ ከተማም ከተማን፥ መንግሥትም መንግሥትን ይወጋል።
3 ፤ የግብጽም መንፈስ በውስጥዋ ባዶ ይሆናል፥ ምክራቸውንም አጠፋለሁ፤ እነርሱም ጣዖቶቻቸውን በድግምት የሚጠነቍሉትንም መናፍስት ጠሪዎቻቸውንም ጠንቋዮቻቸውንም ይጠይቃሉ።
4 ፤ ግብጻውያንንም በጨካኝ ጌታ እጅ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ጨካኝ ንጉሥም ይገዛቸዋል ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
5 ፤ ውኆችም ከባሕር ይደርቃሉ፥ ወንዙም ያንሳል ደረቅም ይሆናል።
6 ፤ ወንዞቹም ይገማሉ፥ የግብጽም መስኖች ያንሳሉ ይደርቃሉም፤ ደንገልና ቄጤማ ይጠወልጋሉ።
7 ፤ በዓባይ ወንዝ ዳር ያለው መስክ በዓባይም ወንዝ አጠገብ የተዘራ እርሻ ሁሉ ይደርቃል፥ ይበተንማል፥ አይገኝምም።
8 ፤ ዓሣ አጥማጆቹ ያዝናሉ፥ በዓባይም ወንዝ መቃጥን የሚጥሉት ሁሉ ያለቅሳሉ፥ በውኆችም ላይ መረብ የሚዘረጉት ይዝላሉ።
9 ፤ የተበጠረውንም የተልባ እግር የሚሠሩ፥ ነጩንም ልብስ የሚሠሩ ሸማኔዎች ያፍራሉ።
10 ፤ ደገፋዎችዋም ሁሉ ይሰባበራሉ፥ የደመወዘኞችም ነፍስ ትተክዛለች።
11 ፤ የጣኔዎስ አለቆች ፍጹም ሰነፎች ናቸው፤ ፈርዖንን የሚመክሩ ጥበበኞች ምክራቸው ድንቍርና ሆነች። ፈርዖንን። እኛ የጥበበኞች ልጆች የቀደሙም ነገሥታት ልጆች ነን እንዴት ትሉታላችሁ?
12 ፤ አሁንሳ ጥበበኞችህ የት አሉ? አሁን ይንገሩህ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በግብጽ ላይ ያሰበውን ይወቁ።
13 ፤ የጣኔዎስ አለቆች ሰነፎች ሆነዋል፥ የሜምፎስም አለቆች ተሸንግለዋል፤ የነገዶችዋ የማዕዘን ድንጋዮች የሆኑ ግብጽን አሳቱ።
14 ፤ እግዚአብሔር የጠማምነትን መንፈስ በውስጥዋ ደባልቆአል፤ ሰካር በትፋቱ እንዲስት እንዲሁ ግብጽን በሥራዋ ሁሉ አሳቱ።
15 ፤ ራስ ወይም ጅራት የሰሌን ቅርንጫፍ ወይም እንግጫ ቢሆን ሊሠራ የሚችል ሥራ ለግብጽ አይሆንላትም።
16 ፤ በዚያ ቀን ግብጻውያን እንደ ሴቶች ይሆናሉ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ ከሚያንቀሳቅሳት ከእጁ መንቀሳቀስ የተነሣ ይሸበራሉ ይፈሩማል።
17 ፤ የይሁዳም ምድር ግብጽን የምታስደነግጥ ትሆናለች፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከመከረባት ምክር የተነሣ ወሬዋን የሚሰማ ሁሉ ይፈራል።
18 ፤ በዚያ ቀን በግብጽ ምድር በከነዓን ቋንቋ የሚናገሩ፥ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔርም የሚምሉ አምስት ከተሞች ይሆናሉ፤ ከነዚህም አንዲቱ የጥፋት ከተማ ተብላ ትጠራለች።
19 ፤ በዚያ ቀን በግብጽ ምድር መካከል ለእግዚአብሔር መሠዊያ፥ በዳርቻዋም ለእግዚአብሔር ዓምድ ይሆናል።
20 ፤ ይህም ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር በግብጽ ምድር ምልክትና ምስክር ይሆናል፤ ከሚያስጨንቁአቸው የተነሣ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉና፥ እርሱም መድኃኒትንና ኃያልን ሰድዶ ያድናቸዋልና።
21 ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር በግብጽ የታወቀ ይሆናል፥ ግብጽAውያንም እግዚአብሔርን ያውቃሉ፤ በመሥዋዕትና በቍርባን ያመልካሉ፥ ለእግዚአብሔርም ስእለት ይሳላሉ ይፈጽሙትማል።
22 ፤ እግዚአብሔርም ግብጽን ይመታታል፤ ይመታታል ይፈውሳታልም፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለሳሉ እርሱም ይለመናቸዋል ይፈውሳቸውማል።
23 ፤ በዚያ ቀን ከግብጽ ወደ አሦር መንገድ ይሆናል፥ አሦራዊውም ወደ ግብጽ፥ ግብጻዊውም ወደ አሦር ይገባል፤ ግብጻውያንም ከአሦራውያን ጋር ይሰግዳሉ።
24
25 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። ሕዝቤ ግብጽ፥ የእጄም ሥራ አሦር፥ ርስቴም እስራኤል የተባረከ ይሁን ብሎ ይባርካቸዋልና በዚያ ቀን እስራኤል ለግብጽና ለአሦር ሦስተኛ ይሆናል፥ በምድርም መካከል በረከት ይሆናል።