ምዕራፍ 21

በባሕር አጠገብ ስላለው ስለ ምድረ በዳ የተነገረ ሸክም። ዐውሎ ነፋስ ከደቡብ እንደሚወጣ፥ እንዲሁ ከሚያስፈራ አገር ከምድረ በዳ ይወጣል።
2 ፤ ከባድ ራእይ ተነገረኝ፤ ወንጀለኛው ይወነጅላል አጥፊውም ያጠፋል። ኤላም ሆይ፥ ውጪ፤ ሜዶን ሆይ፥ ክበቢ፤ ትካዜውን ሁሉ አስቀርቻለሁ።
3 ፤ ስለዚህ ወገቤ ሕመም ተሞላ፤ እንደምትወልድ ሴት ምጥ ያዘኝ፤ ከሕመሜ የተነሣ አልሰማም፥ ከድንጋጤም የተነሣ አላይም።
4 ፤ ልቤ ተንበደበደ፥ ድንጋጤ አስፈራኝ፥ ተስፋ ያደረግሁትም ድንግዝግዝታ መንቀጥቀጥ ሆነብኝ።
5 ፤ ማዕዱን ያዘጋጃሉ፥ ምንጣፉንም ይዘረጋሉ፥ ይበሉማል፥ ይጠጡማል፤ እናንተ መሳፍንት ሆይ፥ ተነሡ፥ ጋሻውን አዘጋጁ።
6 ፤ ጌታ እንዲህ ብሎኛልና። ሂድ ጉበኛም አቁም፥ የሚያየውንም ይናገር።
7 ፤ በከብት የሚቀመጡትን፥ ሁለት ሁለት እየሆኑ የሚሄዱት ፈረሰኞች፥ በአህዮች የሚቀመጡትንና በግመሎች የሚቀመጡትን ባየ ጊዜ በጽኑ ትጋት አስተውሎ ተግቶም ያድምጥ።
8 ፤ ያየውም። ጌታ ሆይ፥ ቀኑን ሁሉ ዘወትር በማማ ላይ ቆሜአለሁ፥ ሌሊቱንም ሁሉ በመጠበቂያዬ ላይ ተተክያለሁ፥
9 ፤ እነሆም፥ በፈረሶች የሚቀመጡ፥ ሁለት ሁለት ሁነው የሚሄዱ ፈረሰኞች ይመጣሉ ብሎ ጮኸ፤ እርሱም መልሶ። ባቢሎን ወደቀች ወደቀች፥ የተቀረጹም የአማልክቶችዋ ምስሎች ሁሉ በምድር ላይ ተጥለው ደቀቁ አለ።
10 ፤ እናንተ በአውድማዬ ላይ የተወቃችሁ የአውድማዬ ልጆች ሆይ፥ ከእስራኤል አምላክ ከሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሰማሁትን ነገርኋችሁ።
11 ፤ ስለ ኤዶምያስ የተነገረ ሸክም። አንዱ ከሴይር። ጕበኛ ሆይ፥ ሌሊቱ ምን ያህል ነው? ጕበኛ ሆይ፥ ሌሊቱ ምን ያህል ነው? ብሎ ጠራኝ።
12 ፤ ጕበኛውም። ይነጋል ድግሞም ይመሻል፤ ትጠይቁ ዘንድ ብትወድዱ ጠይቁ፤ ተመልሳችሁም ኑ አለ።
13 ፤ ስለ ዓረብ የተነገረ ሸክም። የድዳናውያን ነጋዴዎች ሆይ፥ በዓረብ ዱር ውስጥ ታድራላችሁ።
14 ፤ በቴማን የምትኖሩ ሆይ፥ ወደ ተጠሙት ሰዎች ውኃ አምጡ እንጀራ ይዛችሁ የሸሹትን ሰዎች ተቀበሉአቸው።
15 ፤ ከሰይፍ፥ ከተመዘዘው ሰይፍ፥ ከተለጠጠውም ቀስት ከጽኑም ሰልፍ ሸሽተዋልና።
16 ፤ ጌታ እንዲህ ብሎኛልና። እንደ ምንደኛ ዓመት በአንድ ዓመት ውስጥ የቄዳር ክብር ሁሉ ይጠፋል፤
17 ፤ ከቀስተኞች ቍጥር የቀሩት፥ የቄዳር ልጆች ኃያላን፥ ያንሳሉ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።