ምዕራፍ 56

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ማዳኔ ሊመጣ ጽድቄም ሊገለጥ ቀርቦአልና ፍርድን ጠብቁ ጽድቅንም አድርጉ።
2 ፤ ይህን የሚያደርግ ሰው ይህንንም የሚይዝ የሰው ልጅ፥ እንዳያረክሰው ሰንበትንም የሚጠብቅ እጁንም ክፋት ከማድረግ የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።
3 ፤ ወደ እግዚአብሔርም የተጠጋ መጻተኛ። በእውነት እግዚአብሔር ከሕዝቡ ይለየኛል አይበል፤ ጃንደረባም። እነሆ፥ እኔ ደረቅ ዛፍ ነኝ አይበል።
4 ፤ እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና።
5 ፤ በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ።
6 ፤ ያገለግሉት ዘንድ የእግዚአብሔርንም ስም ይወድዱ ዘንድ ባሪያዎቹም ይሆኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር የሚጠጉትንም መጻተኞች፥ እንዳያረክሱት ሰንበትን የሚጠብቁትን ቃል ኪዳኔንም የሚይዙትን ሁሉ፥
7 ፤ ወደ ተቀደሰ ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፥ በጸሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ፤ ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የሚሆን የጸሎት ቤት ይባላልና የሚቃጠለውን መሥዋዕታቸውንና ሌላ መሥዋዕታቸውን በመሠዊያዬ ላይ እቀበላለሁ።
8 ፤ ከእስራኤል የተበተኑትን የሚሰበስብ ጌታ እግዚአብሔር። ወደ ተሰበሰቡት ዘንድ ሌሎችን እሰበስብለታለሁ ይላል።
9 ፤ እናንተ የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ፥ እናንተም የዱር አራዊት ሁሉ፥ ትበሉ ዘንድ ቅረቡ።
10 ፤ ጕበኞቹ ዕውሮች ናቸው፥ ሁሉ ያለ እውቀት ናቸው፤ ሁሉም ዲዳ የሆኑ ውሾች ናቸው ይጮኹም ዘንድ አይችሉም፤ ሕልምን ያልማሉ፤ ይተኛሉ፤ ማንቀላፋትንም ይወድዳሉ።
11 ፤ መብል ወዳጆች ከቶ የማይጠግቡ ውሾች ናቸው፥ እነርሱም ያስተውሉ ዘንድ የማይችሉ እረኞች ናቸው፤ ሁሉ ወደ መንገዳቸው፥ ከፊተኛው እስከ ኋለኛው ድረስ ሁሉ፥ እያንዳንዳቸው ወደ ጥቅማቸው ዘወር ብለዋል።
12 ፤ ኑ የወይን ጠጅ እንውሰድ፥ በሚያሰክርም መጠጥ እንርካ፤ ዛሬም እንደ ሆነ እንዲሁ ነገ ይሆናል፥ ከዛሬም ይልቅ እጅግ ይበልጣል ይላሉ።