ምዕራፍ 65

ላልጠየቁኝ ተገለጥሁ፥ ላልፈለጉኝም ተገኘሁ፤ በስሜም ያልተጠራውን ሕዝብ። እነሆኝ፥ እነሆኝ አልሁት።
2 ፤ መልካም ባልሆነው መንገድ፥ አሳባቸውን እየተከተሉ፥ ወደሚሄዱ ወደ ዓመፀኛ ሕዝብ ቀኑን ሁሉ እጆቼን ዘረጋሁ።
3 ፤ ይህ ሕዝብ ዘወትር የሚያስቈጡኝ ናቸው፤ እነርሱ በአትክልት ውስጥ የሚሠዉ በጡብም ላይ የሚያጥኑ፥
4 ፤ በመቃብርም መካከል የሚቀመጡ፥ በስውርም ስፍራ የሚያድሩ፥ የእሪያ ሥጋም የሚበሉ ናቸው። የረከሰው መረቅ በዕቃቸው ውስጥ አለ።
5 ፤ እነርሱም። ለራስህ ቁም፥ እኔ ከአንተ ይልቅ ቅዱስ ነኝና ወደ እኔ አትቅረብ ይላሉ፤ እነዚህ በአፍንጫዬ ዘንድ ጢስ ቀኑንም ሁሉ የምትነድድ እሳት ናቸው።
6 ፤ እነሆ፥ በፊቴ ተጽፎአል። ኃጢአታችሁና የአባቶቻችሁን ኃጢአት በአንድ ላይ ወደ ብብታቸው ፍዳ አድርጌ አመልሳለሁ እንጂ ዝም አልልም፥ ይላል እግዚአብሔር፤
7 ፤ በተራሮችም ላይ ስላጠኑ፥ በኮረብቶችም ላይ ስለ ሰደቡኝ፥ ስለዚህ አስቀድመው የሠሩትን ሥራቸውን በብብታቸው እሰፍራለሁ።
8 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ወይን በዘለላው በተገኘች ጊዜ። በረከት በእርስዋ ላይ አለና አታጥፉት እንደሚባለው፥ ሁሉን እንዳላጠፉ ስለባሪያዎቼ እንዲሁ አደርጋለሁ።
9 ፤ ከያዕቆብ ዘርን ከይሁዳም ተራሮቼን የሚወርሰውን አወጣለሁ፤ እኔም የመረጥኋቸው ይወርሱአታል፥ ባሪያዎቼም በዚያ ይኖራሉ።
10 ፤ ሳሮንም የበጎች ማሰማርያ፥ የአኮርም ሸለቆ የላሞች መመሰግያ ለፈልጉኝ ሕዝቤ ይሆናል።
11 ፤ እናንተን ግን እግዚአብሔርን የተዋችሁትን፥ ቅዱሱንም ተራራዬን የረሳችሁትን፥ ጉድ ለተባለ ጣዖትም ማዕድ ያዘጋጃችሁትን፥ እድል ለተባለ ጣዖትም የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን የቀዳችሁትን፥
12 ፤ እድላችሁን ለሰይፍ አደርገዋለሁ፥ ሁላችሁም ለመታረድ ትጐነበሳላችሁ፤ በፊቴም ክፉ ነገርን አደረጋችሁ፥ ያልወደድሁትንም መረጣችሁ እንጂ በጠራሁ ጊዜ አልመለሳችሁልኝምና፥ በተናገርሁም ጊዜ አልሰማችሁኝምና።
13 ፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ባሪያዎቼ ይበላሉ እናንተ ግን ትራባላችሁ፤ እነሆ፥ ባሪያዎቼ ይጠጣሉ እናንተ ግን ትጠማላችሁ፤ እነሆ፥ ባሪያዎቼ ደስ ይላቸዋል እናንተ ግን ታፍራላችሁ፤
14 ፤ እነሆ፥ ባሪያዎቼ ከልባቸው ደስታ የተነሣ ይዘምራሉ፥ እናንተ ግን ከልባችሁ ኀዘን የተነሣ ትጮኻላችሁ፥ መንፈሳችሁም ስለ ተሰበረ ወዮ ትላላችሁ።
15 ፤ ስማችሁንም ለተመረጡት ሕዝቤ እርግማን አድርጋችሁ ትተዋላችሁ፥ ጌታ እግዚአብሔርም ይገድላችኋል፥ ባሪያዎቹንም በሌላ ስም ይጠራቸዋል።
16 ፤ እንዲሁም በምድር ላይ የተባረከ በእውነት አምላክ ይባረካል፥ በምድርም ላይ የማለ በእውነት አምላክ ይምላል፤ የቀድሞው ጭንቀት ተረስቶአልና፥ ከዓይኔም ተሰውሮአልና።
17 ፤ እነሆ፥ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እፈጥራለሁና፤ የቀደሙትም አይታሰቡም፥ ወደ ልብም አይገቡም።
18 ፤ ነገር ግን በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘላለምም ሐሤት አድርጉ፤ እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን ለሐሤት፥ ሕዝብዋንም ለደስታ እፈጥራለሁና።
19 ፤ እኔም በኢየሩሳሌም ሐሤት አደርጋለሁ በሕዝቤም ደስ ይለኛል፤ ከዚያም ወዲያ የልቅሶ ድምፅና የዋይታ ድምፅ አይሰማባትም።
20 ፤ ከዚያም ወዲያ ጥቂት ዘመን ብቻ የሚኖር ሕፃን፥ ወይም ዕድሜውን ያልፈጸመ ሽማግሌ አይገኝም፤ ጕልማሳው የመቶ ዓመት ሆኖት ይሞታልና፥ ኃጢአተኛውም የመቶ ዓመት ሆኖት የተረገመ ይሆናልና።
21 ፤ ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ።
22 ፤ ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፥ ሌላም እንዲበላው አይተከሉም፤ የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናልና፥ እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና።
23 ፤ እነርሱ ከነልጆቻቸው የእግዚአብሔር ቡሩካን ዘር ናቸውና በከንቱ አይደክሙም ለጥፋትም አይወልዱም።
24 ፤ እንዲህም ይሆናል፤ ሳይጠሩ አመልስላቸዋለሁ፥ ገናም ሲናገሩ እሰማለሁ።
25 ፤ ተኵላና ጠቦት በአንድነት ይሰማራሉ፥ አንበሳም እንደ በሬ ገለባ ይበላል፥ የእባብም መብል ትቢያ ይሆናል። በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ አይጐዱም፥ አያጠፉምም፥ ይላል እግዚአብሔር።