ምዕራፍ 20

የአሦር ንጉሥ ሳርጎን ተርታንን በሰደደ ጊዜ እርሱም ወደ አዛጦን በመጣ ጊዜ አዛጦንም ወግቶ በያዛት ጊዜ፥
2 ፤ በዚያ ዓመት እግዚአብሔር የአሞጽን ልጅ ኢሳይያስን። ሂድ፥ ማቅህን ከወገብህ አውጣ ጫማህንም ከእግርህ አውልቅ ብሎ ተናገረው። እንዲህም አደረገ፥ ራቁቱንም ባዶ እግሩንም ሄደ።
3 ፤ እግዚአብሔርም አለ። ባሪያዬ ኢሳይያስ በግብጽና በኢትዮጵያ ላይ ሦስት ዓመት ለምልክትና ለተአምራት ሊሆን ራቁቱንና ባዶ እግሩን እንደ ሄደ፥
4 ፤ እንዲሁ የአሦር ንጉሥ የግብጽንና የኢትዮጵያን ምርኮ፥ ጐበዛዝቱንና ሽማግሌዎቹን፥ ራቁታቸውንና ባዶ እግራቸውን አድርጎ ገላቸውንም ገልጦ፥ ለግብጽ ጕስቍልና ይነዳቸዋል።
5 ፤ እነርሱም ከተስፋቸው ከኢትዮጵያ ከትምክሕታቸውም ከግብጽ የተነሣ ይፈራሉ ያፍሩማል፤
6 ፤ በዚያም ቀን በዚች ባሕር ዳርቻ የሚቀመጡ። እነሆ፥ ከአሦር ንጉሥ እንድን ዘንድ ለእርዳታ ወደ እነርሱ የሸሸንበት ተስፋችን ይህ ነበረ፤ እኛስ እንዴት እናመልጣለን? ይላሉ።