ምዕራፍ 7

እንዲህም ሆነ፤ በይሁዳ ንጉሥ በዖዝያን ልጅ በኢዮአታም ልጅ በአካዝ ዘመን የሶርያ ንጉሥ ረአሶን የእስራኤልም ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፥ ሊያሸንፉአትም አልቻሉም።
2 ፤ ለዳዊትም ቤት። ሶርያ ከኤፍሬም ጋር ተባብረዋል የሚል ወሬ ተነገረ፤ የእርሱም ልብ የሕዝቡም ልብ የዱር ዛፍ በነፋስ እንድትናወጥ ተናወጠ።
3 ፤ እግዚአብሔርም ኢሳይያስን አለው። አንተና ልጅህ ያሱብ አካዝን ትገናኙት ዘንድ በልብስ አጣቢው እርሻ መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኵሬ መስኖ ጫፍ ውጡ፤
4 ፤ እንዲህም በለው። ተጠበቅ፥ ዝምም በል፤ ስለ እነዚህ ስለሚጤሱ ስለ ሁለት የእንጨት ጠለሸቶች፥ ስለ ሶርያና ስለ ረአሶን ስለ ሮሜልዩም ልጅ ቍጣ አትፍራ፥ ልብህም አይድከም።
5
6 ፤ ሶርያና ኤፍሬም የሮሜልዩም ልጅ። ወደ ይሁዳ እንውጣ እናስጨንቀውም፥ እንስበረውም፥ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥበት ብለው ክፋት ስለ መከሩብህ፤
7 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ይህ ምክር አይጸናምና አይሆንም።
8 ፤ የሶርያ ራስ ደማስቆ ነው፥ የደማስቆም ራስ ረአሶን ነው፤ በስድሳ አምስት ዓመት ውስጥ ኤፍሬም ይሰባበራልና ሕዝብ አይሆንም፤
9 ፤ የኤፍሬምም ራስ ሰማርያ ነው፥ የሰማርያም ራስ የሮሜልዩ ልጅ ነው። ባታምኑ አትጸኑም።
10 ፤ እግዚአብሔርም ደግሞ አካዝን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
11 ፤ ከጥልቁ ወይም ከከፍታው ቢሆን ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ምልክትን ለምን።
12 ፤ አካዝም። አልለምንም፥ እግዚአብሔርንም አልፈታተንም አለ።
13 ፤ እርሱም አለ። እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፥ ስሙ፤ በውኑ ሰውን ማድከማችሁ ቀላል ነውን? አምላኬን ደግሞ የምታደክሙ፤
14 ፤ ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።
15 ፤ ክፉን ለመጥላት መልካሙንም ለመምረጥ ሲያውቅ ቅቤና ማር ይበላል።
16 ፤ ሕፃኑ ክፉን ለመጥላት መልካሙን ለመምረጥ ሳያውቅ የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት አገር ባድማ ትሆናለች።
17 ፤ እግዚአብሔርም ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ ያልመጣውን ዘመን በአንተና በሕዝብህ በአባትህም ቤት ላይ ያመጣል፤ እርሱም የአሦር ንጉሥ መምጣት ነው።
18 ፤ በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ እግዚአብሔር በግብጽ ወንዝ ዳርቻ ያለውን ዝምብ በአሦርም አገር ያለውን ንብ በፉጨት ይጠራል።
19 ፤ ይመጡማል፥ እነርሱም ሁሉ በበረሃ ሸለቆ በድንጋይም ዋሻ ውስጥ በእሾህ ቍጥቋጦ ሁሉ ላይ በማሰማርያውም ሁሉ ላይ ይሰፍራሉ።
20 ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ከወንዙ ማዶ በተከራየው ምላጭ በአሦር ንጉሥ የራሱንና የእግሩን ጠጕር ይላጨዋል፤ ምላጩም ጢሙን ደግሞ ይበላል።
21 ፤ በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሰው አንዲት ጊደርን ሁለት በጎችንም ያሳድጋል፤
22 ፤ ከሚሰጡት ወተት ብዛት የተነሣ ቅቤ ይበላል፤ በአገሪቱም መካከል የቀረ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላል።
23 ፤ በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሺህ ብር የተገመተ ሺህ የወይን ግንድ በነበረበት ስፍራ ሁሉ ለኵርንችትና ለእሾህ ይሆናል።
24 ፤ ኵርንችትና እሾህ በምድር ሁሉ ላይ ነውና በፍላጻና በቀስት ወደዚያ ይገባሉ።
25 ፤ በመቈፈርያም ወደ ተቈፈሩ ኮረብቶች ሁሉ ከኵርንችትና እሾህ ፍርሃት የተነሣ ወደዚያ አትሄድም፤ ነገር ግን የበሬ ማሰማርያና የበግ መራገጫ ይሆናል።