ምዕራፍ 38

በዚያም ወራት ሕዝቅያስ ለሞት እስኪደርስ ታመመ። ነቢዩም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ወደ እርሱ መጥቶ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ትሞታለህ እንጂ በሕይወት አትኖርምና ቤትህን አስተካክል አለው።
2 ፤ ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ።
3 ፤ አቤቱ፥ በፊትህ በእውነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ ታስብ ዘንድ እለምንሃለሁ። ሕዝቅያስም እጅግ አድርጎ አለቀሰ።
4 ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል መጣ።
5 ፤ ሂድ፥ ሕዝቅያስን እንዲህ በለው። የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጸሎትህን ሰምቻለሁ፥ እንባህንም አይቻለሁ፤ እነሆ፥ በዕድሜህ ላይ አሥራ አምስት ዓመት አጨምራለሁ።
6 ፤ አንተንና ይህችንም ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፥ ይህችንም ከተማ እጋርዳታለሁ።
7 ፤ እግዚአብሔርም የተገረውን ነገር እንዲፈጽመው ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክቱ ይህ ይሆንልሃል።
8 ፤ እነሆ፥ በአካዝ የጥላ ስፍረ ሰዓት ላይ ከፀሐይ ጋር የወረደውን በደረጃዎች ያለውን ጥላ አሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደርጋለሁ። ፀሐይም በጥላ ስፍረ ሰዓት ላይ የወረደበት አሥር ደረጃ ወደ ኋላ ተመለሰ።
9 ፤ የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ታምሞ ከደዌው በተፈወሰ ጊዜ የጻፈው ጽሕፈት ይህ ነው።
10 ፤ እኔ። በሕይወት ዘመኔ መካከል ወደ ሲኦል በሮች እገባለሁ፤ የቀረው ዘመኔ ጐደለብኝ አልሁ።
11 ፤ ደግሞም። በሕያዋን ምድር እግዚአብሔርን አላይም፤ በዓለምም ከሚኖሩ ጋር ሰውን እንግዲህ አልመለከትም አልሁ።
12 ፤ ማደሪያዬ ተነቀለች፥ እንደ እረኛ ድንኳንም ከእኔ ዘንድ ተወገደች፤ ሕይወቴንም እንደ ሸማኔ ጠቀለልሁ፥ እርሱም ከመጠቅለያው ይቈርጠኛል፤ ከማለዳም ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ታጠፋኛለህ።
13 ፤ እስኪነጋ ድረስ ቈይቼ ነበር፤ እርሱ እንደ አንበሳ አጥንቴን ሁሉ ሰበረ፤ ከማለዳ ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ታጠፋኛለህ።
14 ፤ እንደ ጨረባና እንደ ሽመላ ተንጫጫሁ፥ እንደ ርግብም አጕረመረምሁ፤ ዓይኖቼ ወደ ላይ ከማየት ደከሙ። ጌታ ሆይ፥ ተጨንቄአለሁና መከታ ሁነኝ።
15 ፤ ምን እላለሁ? እርሱ ተናግሮኛል፥ እርሱ ራሱም ይህን አድርጎአል፤ በዘመኔ ሁሉ ስለ ነፍሴ ምሬት ቀስ ብዬ እሄዳለሁ።
16 ፤ ጌታ ሆይ፥ በዚህ ነገር ሰዎች በሕይወት ይኖራሉ፥ በዚህም ሁሉ የመንፈሴ ሕይወት ነው፤ አንተም ፈወስኸኝ ወደ ሕይወትም መለስኸኝ።
17 ፤ እነሆ፥ ታላቅ ምሬት ለደኅንነቴ ሆነ፤ አንተም ነፍሴን ከጥፋት ጕድጓድ አዳንሃት፥ ኃጢአቴንም ሁሉ ወደ ኋላህ ጣልህ።
18 ፤ ሲኦል አያመሰግንህምና፥ ሞትም አያከብርህምና፤ ወደ ጕድጓዱ የሚወርዱ እውነትህን ተስፋ አያደርጉም።
19 ፤ እኔ ዛሬ አንደማደርግ ሕያዋን እነርሱ ያመሰግኑሃል፤ አባት ለልጆች እውነትህን ያስታውቃል።
20 ፤ እግዚአብሔር ያድነኛል፤ ስለዚህ በዕድሜያችን ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ቅኔዎችን አውታር ባለው ዕቃ እንዘምራለን።
21 ፤ ኢሳይያስም። የበለስ ጥፍጥፍ አምጥተው በእባጩ ላይ ይለብጡት፥ እርሱም ይፈወሳል ብሎ ነበር።
22 ፤ ሕዝቅያስም። ወደ እግዚአብሔር ቤት እወጣ ዘንድ ምልክቱ ምንድር ነው? ብሎ ነበር።