ትንቢተ ኢሳይያስ
ምዕራፍ 15
ስለ ሞዓብ የተነገረ ሸክም። የሞዓብ ዔር በሌሊት ፈርሶ ጠፋ፤ ቂር የሚባልም የሞዓብ ምሽግ በሌሊት ፈርሶ ጠፋ።
2 ፤ ወደ ባይት ወደ ዲቦንም ወደ ኮረብታ መስገጃዎችም ለልቅሶ ወጥተዋል፤ ሞዓብ በናባው በሜድባ ላይ ታለቅሳለች፤ ራሳቸው ሁሉ ተነጭቶአል፥ ጢማቸውም ሁሉ ተላጭቶአል።
3 ፤ በየመገዳቸውም በማቅ ታጥቀዋል፤ በየሰገነቶቻቸውና በየአደባባዮቻቸው እንባ እጅግ እያፈሰሱ ሁሉም አልቅሰዋል።
4 ፤ ሐሴቦንና ኤልያሊ ጮኹ፤ ድምፃቸው እስከ ያሀጽ ድረስ ይሰማል፤ ስለዚህ የሞዓብ ሰልፈኞች ጮኹ፤ ነፍስዋ በውስጥዋ ተንቀጠቀጠች።
5 ፤ ልቤ ስለ ሞዓብ ጮኸ፤ ከእርስዋም የሚሸሹ ወደ ዞዓር ወደ ዔግላት ሺሊሺያ ኰበለሉ፤ በሉሒት ዓቀበት ላይ እያለቀሱ ይወጣሉ፥ በሖሮናይምም መንገድ የዋይታ ጩኸት ያነሣሉ።
6 ፤ የኔምሬም ውኆች ይደርቃሉ፤ ሣሩም ደርቋል፥ ለጋውም ጠውልጓል፥ ልምላሜውም ሁሉ የለም።
7 ፤ ስለዚህ የሰበሰቡትን ሀብትና መዝገባቸውን ወደ አኻያ ዛፍ ወንዝ ማዶ ይወስዱታል።
8 ፤ ጩኸት የሞዓብን ዳርቻ ሁሉ ዞረ፤ ልቅሶዋም ወደ ኤግላይምና ወደ ብኤርኢሊም ደረሰ።
9 ፤ የዲሞንም ውኃ ደም ተሞልታለች፤ በዲሞንም ላይ ሥቃይን እጨምራለሁ፥ ከሞዓባውያንም በሚያመልጡ፥ ከምድርም በሚቀሩ ላይ አንበሳን አመጣለሁ።