ምዕራፍ 23

ስለ ጢሮስ የተነገረ ሸክም። የተርሴስ መርከቦች ሆይ፥ አልቅሱ፤ ፈርሶአልና ቤት የለም፥ መግባትም የለም፤ ከኪቲም አገር ጀምሮ ተገልጦላቸዋል።
2 ፤ እናንተ በደሴት የምትኖሩ በባሕርም የምትሻገሩ የሲዶና ነጋዴዎች ንግድ የሞሉባችሁ ሆይ፥ ጸጥ በሉ።
3 ፤ የሺሖር ዘርና የዓባይ ወንዝ መከር በብዙ ውኆች ላይ ገቢዋ ነበረ፤ እርስዋም የአሕዛብ መናገጃ ነበረች።
4 ፤ ሲዶና ሆይ፥ ባሕር፥ የባሕር ምሽግ። አላማጥሁም፥ አልወለድሁም፤ ጐበዛዝትንም አላሳደግሁም፥ ደናግልንም አላሳደግሁም ብሎ ተናግሮአልና እፈሪ።
5 ፤ ወሬዋ ወደ ግብጽ በደረሰ ጊዜ በጢሮስ ወሬ ምጥ ይይዛቸዋል።
6 ፤ ወደ ተርሴስ ተሻገሩ፤ እናንተ በደሴት የምትኖሩ አልቅሱ።
7 ፤ በቀድሞ ዘመን ተመሥርታ የነበረችው፥ በዚያም እንደ እንግዳ ሆና ትኖር ዘንድ እግሮችዋ ወደ ሩቅ ያፈለሱአት የደስታችሁ ከተማ ይህች ናትን?
8 ፤ አክሊል ባስጫነች ከተማ በጢሮስ ላይ ይህን የወሰነ ማን ነው? ነጋዴዎችዋ አለቆች ናቸው፥ በእርስዋም የሚሸጡና የሚለውጡ የምድር ክቡራን ናቸው።
9 ፤ የክብርን ሁሉ ትዕቢት ይሽር ዘንድ የምድርንም ክቡራን ሁሉ ያስንቅ ዘንድ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወስኖታል።
10 ፤ የተርሴስ ልጅ ሆይ፥ የሚከለክልሽ የለምና እንደ ዓባይ ወንዝ በአገርሽ ላይ ጐርፈሽ እለፊ።
11 ፤ በባሕር ላይ እጁን ዘረጋ መንግሥታትንም አናወጠ፤ ምሽጎችዋንም ያጠፉ ዘንድ እግዚአብሔር ስለ ከነዓን አገር አዘዘ።
12 ፤ እርሱም። አንቺ የተበደልሽ የሲዶና ድንግል ልጅ ሆይ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ደስ አይበልሽ፤ ተነሥተሽ ወደ ኪቲም ተሻገሪ፥ በዚያም ደግሞ አታርፊም አለ።
13 ፤ እነሆ፥ የከለዳውያን አገር! ይህ ሕዝብ ሆኖ አይገኝም፤ አሦራውያን ለምድረ በዳ አራዊት ሰጥተውታል፤ ግንቦቻቸውን ሠሩ፥ አዳራሾችዋንም አፈረሱ፥ ባድማም አደረጓት።
14 ፤ እናንተ የተርሴስ መርከቦች ሆይ፥ ምሽጋችሁ ፈርሶአልና ዋይ በሉ።
15 ፤ በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ጢሮስ እንደ አንድ ንጉሥ ዘመን ሰባ ዓመት ያህል የተረሳች ትሆናለች፤ ከሰባ ዓመት በኋላ ግን ለጢሮስ በጋለሞታ ዘፈን እንደሚሆን እንዲሁ ይሆናል።
16 ፤ አንቺ የተረሳሽ ጋለሞታ ሆይ፥ መሰንቆ ያዢ በከተማ ላይም ዙሪ፤ መታሰቢያም ይሆንልሽ ዘንድ ዜማን አሳምሪ ዘፈንሽንም አብዢ።
17 ፤ ከሰባ ዓመትም በኋላ እግዚአብሔር ጢሮስን ይጐበኛታል፥ ወደ ዋጋዋም ትምለሳለች፥ ደግሞም በምድር ፊት ላይ ከሆኑ ከዓለም መንግሥታት ሁሉ ጋር ትገለሙታለች።
18 ፤ ንግድዋና ዋጋዋ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፤ ንግድዋም በልተው ይጠግቡ ዘንድ ማለፊያም ልብስ ይለብሱ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ለሚኖሩ ይሆናል እንጂ በዕቃ ቤትና በግምጃ ቤት ውስጥ አይከተትም።