ምዕራፍ 49

ደሴቶች ሆይ፥ ስሙኝ፥ እናንተም በሩቅ ያላችሁ አሕዛብ፥ አድምጡ፤ እግዚአብሔር ከማኅፀን ጠርቶኛል፥ ከእናቴም ሆድ ጀምሮ ስሜን አንሥቶአል፤
2 ፤ አፌንም እንደ ተሳለ ሰይፍ አድርጎአል፥ በእጁ ጥላ ሰውሮኛል፤ እንደ ተሳለ ፍላጻም አድርጎኛል፥ በሰገባውም ውስጥ ሽጎኛል።
3 ፤ እርሱም። እስራኤል ሆይ፥ አንተ ባሪያዬ ነህ በአንተም እከበራለሁ አለኝ።
4 ፤ እኔ ግን። በከንቱ ደከምሁ፥ ምንም ጥቅም ለሌለውና ለከንቱ ጕልበቴን ፈጀሁ፤ ፍርዴ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ፥ ዋጋዬም በአምላኬ ዘንድ ነው አልሁ።
5 ፤ አሁንም በእግዚአብሔር ዓይን ከብሬአለሁና፥ አምላኬም ጕልበት ሆኖኛልና ያዕቆብን ወደ እርሱ እንድመልስ እስራኤልንም ወደ እርሱ እንድሰበስብ ባሪያ እሆነው ዘንድ ከማኅፀን ጀምሮ የሠራኝ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።
6 ፤ እርሱም። የያዕቆብን ነገዶች እንድታስነሣ ከእስራኤልም የዳኑትን እንድትመስል ባሪያዬ ትሆን ዘንድ እጅግ ቀላል ነገር ነውና እስከ ምድር ዳር ድረስ መድኃኒት ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌ ሰጥቼሃለሁ ይላል።
7 ፤ የእስራኤል ታዳጊ ቅዱሱም፥ እግዚአብሔር፥ ሰዎች ለሚንቁት ሕዝብም ለሚጠላው ለገዥዎች ባሪያ እንዲህ ይላል። ስለ ታማኙ ስለ እግዚአብሔር ስለ መረጠህም ስለ እስራኤል ቅዱስ ነገሥታት አይተው ይነሣሉ፥ መሳፍንትም አይተው ይሰግዳሉ።
8 ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በተወደደ ጊዜ ሰምቼሃለሁ፥ በመድኃኒትም ቀን ረድቼሃለሁ፤ እጠብቅህማለሁ፥ ምድርንም ታቀና ዘንድ፥ ውድማ የሆኑትንም ርስቶች ታወርስ ዘንድ፥
9 ፤ የተጋዙትንም። ውጡ በጨለማም የተቀመጡትን። ተገለጡ ትል ዘንድ ቃል ኪዳን አድርጌ ለሕዝቡ ሰጥቼሃለሁ። በመንገድም ላይ ይሰማራሉ፥ ማሰማርያቸውም በወና ኮረብታ ሁሉ ላይ ይሆናል።
10 ፤ የሚራራላቸውም ይመራቸዋልና፥ በውኃም ምንጮች በኩል ይነዳቸዋልና አይራቡም፥ አይጠሙም፥ ትኩሳት ወይም ፀሐይ አይጐዳቸውም።
11 ፤ ተራሮቼንም ሁሉ መንገድ አደርጋለሁ፥ ጎዳኖቼም ከፍ ከፍ ይላሉ።
12 ፤ እነሆ፥ እነዚህ ከሩቅ፥ እነሆም፥ እነዚህ ከሰሜንንና ከምዕራብ፥ እነዚህም ከሲኒም አገር ይመጣሉ።
13 ፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን አጽናንቶአልና፥ ለችግረኞቹም ራርቶአልና ሰማያት ሆይ፥ ዘምሩ፥ ምድር ሆይ፥ ደስ ይበልሽ ተራሮችም ሆይ፥ እልል በሉ።
14 ፤ ጽዮን ግን። እግዚአብሔር ትቶኛል ጌታም ረስቶኛል አለች።
15 ፤ በውኑ ሴት ከማኅፀንዋ ለተወለደው ልጅ እስከማትራራ ድረስ ሕፃንዋን ትረሳ ዘንድ ትችላለችን? አዎን፥ እርስዋ ትረሳ ይሆናል፥ እኔ ግን አልረሳሽም።
16 ፤ እነሆ፥ እኔ በእጄ መጻፍ ቀርጬሻለሁ፥ ቅጥሮችሽም ሁልጊዜ በፊቴ አሉ።
17 ፤ ልጆችሽ ይፈጥናሉ፤ ያፈረሱሽና ያወደሙሽ ከአንቺ ዘንድ ይወጣሉ።
18 ፤ ዓይንሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ እነዚህ ሁሉ ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ። እኔ ሕያው ነኝና እነዚህን ሁሉ እንደ ጌጥ ትለብሻቸዋለሽ፥ እንደ ሙሽራም ትጐናጸፊአቸዋለሽ፥ ይላል እግዚአብሔር።
19 ፤ ባድማሽና ውድማሽ ወናም የሆነው ምድርሽ ከሚኖሩብሽ የተሣ ዛሬ ጠባብ ትሆናለችና፥ የዋጡሽም ይርቃሉና።
20 ፤ የወላድ መካን ከሆንሽ በኋላ የተወለዱልሽ ልጆችሽ በጆሮሽ። ስፍራ ጠብቦኛልና እቀመጥ ዘንድ ቦታ አስፊልኝ ይላሉ።
21 ፤ አንቺም በልብሽ፥ የወላድ መካን ሆኛለሁና፥ እኔም ብቻዬን ተሰድጄአለሁና ተቅበዝበዤ አለሁምና እነዚህን ማን ወለደልኝ? እነዚህንስ ማን አሳደጋቸው? እነሆ፥ ብቻዬን ቀርቼ ነበር፤ እነዚህስ ወዴት ነበሩ? ትያለሽ።
22 ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ እጄን ወደ አሕዛብ አነሣለሁ፥ ዓለማዬንም ወደ ወገኖች አቆማለሁ፤ ወንዶች ልጆችሽንም በብብታቸው ያመጡአቸዋል፥ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃቸው ላይ ይሸከሙአቸዋል።
23 ፤ ነገሥታትም አሳዳጊ አባቶችሽ ይሆናሉ፥ እቴጌዎቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይሆናሉ፤ ግምባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል፥ የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ፥ እኔንም በመተማመን የሚጠባበቁ አያፍሩም።
24 ፤ በውኑ ብዝበዛ ከኃያል እጅ ይወሰዳልን? ወይስ የጨካኙ ምርኮኞች ያመልጣሉን?
25 ፤ እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል። በኃያላን የተማረኩ ይወሰዳሉ፥ የጨካኞችም ብዝበዛ ያመልጣል፤ ከአንቺ ጋር የሚጣሉትን እጣላቸዋለሁ፥ ልጆችሽንም አድናለሁ።
26 ፤ አስጨናቂዎችሽንም ሥጋቸውን አስበላቸዋለሁ፥ እንደ ጣፋጭም ወይን ጠጅ ደማቸውን ጠጥተው ይሰክራሉ፤ ሥጋ ለባሹም ሁሉ እኔ እግዚአብሔር መድኃኒትሽና ታዳጊሽ፥ የያዕቆብ ኃያል እንደ ሆንሁ ያውቃል።