ምዕራፍ 62

ስለ ጽዮን ዝም አልልም፥ ስለ ኢየሩሳሌምም ጸጥ አልልም፥ ጽድቅዋ እንደ ጸዳል መዳንዋም እንደሚበራ ፋና እስኪወጣ ድረስ።
2 ፤ አሕዛብም ጽድቅሽን ነገሥታትም ሁሉ ክብርሽን ያያሉ፤ የእግዚአብሔርም አፍ በሚጠራበት በአዲሱ ስም ትጠሪያለሽ።
3 ፤ በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል፥ በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ።
4 ፤ ከእንግዲህ ወዲህ። የተተወች አትባዪም፤ ምድርሽም ከእንግዲህ ወዲህ። ውድማ አትባልም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ብሎታልና፥ ምድርሽም ባል ታገባለችና አንቺ። ደስታዬ የሚኖርባት ትባያለሽ ምድርሽም። ባል ያገባች ትባላለች።
5 ፤ ጕልማሳም ድንግሊቱን እንደሚያገባ፥ እንዲሁ ልጆችሽ ያገቡሻል፤ ሙሽራም በሙሽራይቱ ደስ እንደሚለው፥ እንዲሁ አምላክሽ በአንቺ ደስ ይለዋል።
6
7 ፤ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ጕበኞችን በቅጥርሽ ላይ አቁሜአለሁ፤ ቀንና ሌሊት ከቶ ዝም አይሉም፤ እናንተ እግዚአብሔርን የምታሳስቡ፥ ኢየሩሳሌምን እስኪያጸና በምድርም ላይ ምስጋና እስኪያደርጋት ድረስ አትረፉ ለእርሱም ዕረፍት አትስጡ።
8 ፤ እግዚአብሔር። ከእንግዲህ ወዲህ በእርግጥ ለጠላቶችሽ መብል ይሆን ዘንድ እህልሽን አልሰጥም፥ መጻተኞችም የደከምሽበትን ወይንሽን አይጠጡም፤
9 ፤ ነገር ግን የሰበሰቡት ይበሉታል እግዚአብሔርንም ያመሰግናሉ፥ ያከማቹትም በመቅደሴ አደባባይ ላይ ይጠጡታል ብሎ በቀኙና በኃይሉ ክንድ ምሎአል።
10 ፤ እለፉ፥ በበሮች በኩል እለፉ፤ የሕዝቡንም መንገድ ጥረጉ፤ አዘጋጁ፥ ጐዳናውን አዘጋጁ፥ ድንጋዮቹንም አስወግዱ፤ ለአሕዛብም ዓለማ አንሡ።
11 ፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር ለምድር ዳርቻ አዋጅ እንዲህ ብሎ ነግሮአል። ለጽዮን ልጅ። እነሆ፥ መድኃኒትሽ ይመጣል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ሥራውም በፊቱ አለ በሉአት።
12 ፤ እግዚአብሔር። የተቤዣቸው፥ የተቀደሰ ሕዝብ ብለው ይጠሩአቸዋል፤ አንቺም። የተፈለገች ያልተተወችም ከተማ ትባያለሽ።