ምዕራፍ 3

እነሆ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ድጋፍንና ብርታትን፥ የእንጀራን ድጋፍ ሁሉ የውኃውንም ድጋፍ ሁሉ፥
2 ፤ ኃያሉንም፥ ተዋጊውንም፥ ፈራጁንም፥ ነቢዩንም፥ ምዋርተኛውንም፥
3 ፤ ሽማግሌውንም፥ የአምሳ አለቃውንም፥ ከበርቴውንም፥ አማካሪውንም፥ ብልሁንም ሠራተኛ፥ አስማት አዋቂውንም ይነቅላል።
4 ፤ አለቆቻቸው እንዲሆኑ ብላቴኖችን አስነሣባቸዋለሁ፥ ሕፃናቶችም ይገዙአቸዋል።
5 ፤ ሕዝቡም፥ ሰው በሰው ላይ ሰውም በባልንጀራው ላይ፥ ይገፋፋል፤ ብላቴናውም በሽማግሌው ላይ የተጠቃውም በከበርቴው ላይ ይኰራል።
6 ፤ ሰውም በአባቱ ቤት ውስጥ ወንድሙን ይዞ። አንተ ልብስ አለህ አለቃም ሁንልን ይህችም ባድማ ከእጅህ በታች ትሁን ሲለው፥
7 ፤ በዚያ ቀን ድምፁን ከፍ አድርጎ። እኔ በቤቴ ውስጥ እንጀራ ወይም ልብስ የለኝምና ባለ መድኃኒት አልሆንም፤ በሕዝቡም ላይ አለቃ አታደርጉኝም ይላል።
8 ፤ የክብሩን ዓይን ያስቈጡ ዘንድ ምላሳቸውና ሥራቸው በእግዚአብሔር ላይ ነውና ኢየሩሳሌም ተፈታች ይሁዳም ወደቀ።
9 ፤ የፊታቸውም እፍረት ይመሰክርባቸዋል፤ እንደ ሰዶምም ኃጢአታቸውን ያወራሉ፥ አይሠውሩአትም። በራሳቸው ላይ ክፉ ነገርን ሠርተዋልና ለነፍሳቸው ወዮ!
10 ፤ የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉና ጻድቁን። መልካም ይሆንልሃል በሉት።
11 ፤ እንደ እጁ ሥራ ፍዳው ይደረግበታልና ለበደለኛ ወዮ! ክፉም ደርሶበታል።
12 ፤ ሕዝቤንስ አስገባሪዎቻቸው ይገፉአቸዋል፥ አስጨናቂዎችም ይሠለጥኑባቸዋል። ሕዝቤ ሆይ፥ የመሩአችሁ ያስቱአችኋል የምትሄዱበትንም መንገድ ያጠፋሉ።
13 ፤ እግዚአብሔር ለፍርድ ተነሥቶአል በሕዝቡም ላይ ሊፈርድ ቆሞአል።
14 ፤ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ሽማግሌዎችና ከአለቆቻቸው ጋር ይፋረዳል፤ የወይኑን ቦታ የጨረሳችሁ እናንተ ናችሁ፤ ከድሆች የበዘበዛችሁት በቤታችሁ አለ፤
15 ፤ ሕዝቤንም ለምን ታደቅቁአቸዋላችሁ? የድሆችንስ ፊት ለምን ትፈጫላችሁ? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
16 ፤ ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ አለ። የጽዮን ቈነጃጅት ኰርተዋልና፥ አንገታቸውንም እያሰገጉ በዓይናቸውም እያጣቀሱ፥ ፈንጠርም እያሉ፥ በእግራቸውም እያቃጨሉ ይሄዳሉና
17 ፤ ስለዚህ ጌታ የጽዮንን ቈነጃጅት አናት በቡሀነት ይመታል፥ እግዚአብሔርም ኀፍረተ ሥጋቸውን ይገልጣል።
18 ፤ በዚያም ቀን ጌታ የእግር አልቦውን ክብር፥ መርበብንም፥ ጨረቃ የሚመስለውንም ጌጥ፥ የጆሮ እንጥልጥሉንም፥
19 ፤ አንባሩንም፥ መሸፈኛውንም፥ ቀጸላውንም፥
20 ፤ ሰንሰለቱንም፥ መቀነቱንም፥ የሽቱውንም ዕቃ፥
21 ፤ አሸንክታቡንም፥ የእጅና የአፍንጫ ቀለበቱንም፥
22 ፤ የዓመት በዓልንም ልብስ፥ መጐናጸፊያውንም፥ ልግምበገላውንም፥ ከረጢቱንም፥
23 ፤ መስተዋቱንም፥ ከጥሩ በፍታ የተሰራውንም ልብስ፥ ራስ ማሰሪያውንም፥ ዓይነ ርግቡንም ያስወግዳል።
24 ፤ እንዲህም ይሆናል፤ በሽቱ ፋንታ ግማት፥ በመታጠቂያውም ፋንታ ገመድ፥ ጠጕርንም በመንቀስ ፋንታ ቡሀነት፥ በመጐናጸፊያ ፋንታ ማቅ፥ በውበትም ፋንታ ጠባሳ ይሆናል።
25 ፤ ጕልማሶችሽ በሰይፍ፥ ኃያላንሽም በውጊያ ይወድቃሉ።
26 ፤ በሮችዋ ያዝናሉ ያለቅሱማል፤ እርስዋም ብቻዋን በምድር ላይ ትቀመጣለች።