ምዕራፍ 13

የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ያየው ስለ ባቢሎን የተንገረ ሸክም።
2 ፤ ምድረ በዳ በሆነ ተራራ ላይ ምልክትን አቁሙ፥ ድምፅንም ከፍ አድርጉባቸው፤ በአለቆችም ደጆች እንዲገቡ በእጅ ጥቀሱ።
3 ፤ ቍጣዬን ይፈጽሙ ዘንድ ቅዱሳኔን አዝዣለሁ፥ እኔ ኃያላኔንና በታላቅነቴ ደስ የሚላቸውን ጠርቻለሁ።
4 ፤ በተራሮች ላይ እንደ ታላቅ ሕዝብ ድምፅ የሆነ የብዙ ሰው ድምፅ አለ። የከተማቹት የአህዛብ መንግሥታት የውካታ ጫጫታ አለ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሠራዊትን ለሰልፍ አሰልፎአል።
5 ፤ እግዚአብሔርና የቍጣው የጦር ዕቃ ምድርን ሁሉ ያጠፉአት ዘንድ ከሩቅ አገር ከሰማይ ዳርቻ ይመጣሉ።
6 ፤ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና፥ አልቅሱ፤ ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ እንደሚመጣ ጥፋት ይመጣል።
7 ፤ ስለዚህ እጅ ሁሉ ትዝላለች፥ የሰውም ሁሉ ልብ ይቀልጣል።
8 ፤ ይደነግጣሉ፤ ምጥና ሕማም ይይዛቸዋል፥ እንደምትወልድ ሴትም ያምጣሉ፤ አንዱም በሌላው ይደነቃል፥ ፊታቸውም የነበልባል ፊት ነው።
9 ፤ እነሆ፥ ምድሪቱን ባድማ ሊያደርግ፥ ኃጢአተኞችዋንም ከእርስዋ ዘንድ ሊያጠፋ ጨካኝ ሆኖ በመዓትና በጽኑ ቍጣ ተሞልቶ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል።
10 ፤ የሰማይም ከዋክብትና ሠራዊቱ ብርሃናቸውን አይሰጡም፥ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ትጨልማለች፥ ጨረቃም በብርሃኑ አያበራም።
11 ፤ ዓለሙን ስለ ክፋታቸው ክፉዎቹንም ስለ በደላቸው እቀጣለሁ፤ የትዕቢተኞችንም ኵራት አዋርዳለሁ።
12 ፤ የቀሩትም ከጥሩ ወርቅ ይልቅ የከበሩ ይሆናሉ፥ ሰውም ከኦፊር ወርቅ ይልቅ የከበረ ይሆናል።
13 ፤ ስለዚህ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር መዓት በጽኑ ቍጣ ቀንም ሰማያትን አነቃንቃለሁ፥ ምድርም ከስፍራዋ ትናወጣለች።
14 ፤ እንደ ተባረረም ሚዳቋ፥ ማንም እንደማይሰበስበው እንደ በግ መንጋ፥ ሰው ሁሉ ወደ ወገኑ ይመለሳል፥ ሁሉም ወደ አገሩ ይሸሻል።
15 ፤ የተገኘ ሁሉ የተወጋ ይሆናል፥ የተያዘም ሁሉ በሰይፍ ይወድቃል።
16 ፤ ሕፃናቶቻቸውም በፊታቸው ይጨፈጨፋሉ፥ ቤቶቻቸውም ይበዘበዛሉ፥ ሚስቶቻቸውም ይነወራሉ።
17 ፤ እነሆ፥ ብር የማይሹትን፥ ወርቅም የማያምራቸውን ሜዶናውያንን በላያቸው አስነሣለሁ።
18 ፤ ፍላጾቻቸውም ጎበዞችን ይጨፈጭፋሉ፥ የማኅፀንንም ፍሬ አይምሩም፥ ዓይኖቻቸውም ለሕፃናት አይራሩም።
19 ፤ እግዚአብሔርም ሰዶምንና ገሞራን ባፈረሰ ጊዜ እንደ ነበረው፥ የመንግሥታት ክብር የከለዳውያንም ትዕቢት ጌጥ ባቢሎን እንዲሁ ትሆናለች።
20 ፤ ለዘላለም የሚቀመጥባት አይገኝም፥ ከትውልድ እስከ ትውልድ ድረስ ሰው አይኖርባትም፤ ዓረባውያንም ድንኳንን በዚያ አይተክሉም፥ እረኞችም መንጎቻቸውን በዚያ አያሳርፉም።
21 ፤ በዚያም የምድረ በዳ አራዊት ያርፋሉ፥ ጕጕቶችም በቤቶቻቸው ይሞላሉ፤ ሰጎኖችም በዚያ ይኖራሉ፥ በዚያም አጋንንት ይዘፍናሉ።
22 ፤ ተኵላዎችም በግንቦቻቸው፥ ቀበሮችም በሚያማምሩ አዳራሾቻቸው ይጮኻሉ፤ ጊዜዋም ለመምጣት ቀርቦአል ቀንዋም አይዘገይም።