ምዕራፍ 44

አሁንም ባሪያዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማ።
2 ፤ የፈጠረህ ከማኅፀንም የሠራህ የሚረዳህም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ባሪያዬ ያዕቆብ የመረጥሁህም ይሹሩን ሆይ፥ አትፍራ።
3 ፤ በተጠማ ላይ ውኃን በደረቅም መሬት ላይ ፈሳሾችን አፈስሳለሁና፤ መንፈሴን በዘርህ ላይ በረከቴንም በልጆችህ ላይ አፈስሳለሁ፥
4 ፤ በፈሳሾችም አጠገብ እንደሚበቅሉ እንደ አኻያ ዛፎች በሣር መካከል ይበቅላሉ።
5 ፤ ይህ። እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ይላል፥ ያም በያዕቆብ ስም ይጠራል፤ ይህም። እኔ የእግዚአብሔር ነኝ ብሎ በእጁ ይጽፋል በእስራኤልም የቁልምጫ ስም ይጠራል።
6 ፤ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ፥ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም።
7 ፤ እንደ እኔ ያለ ማን ነው? ይነሣና ይጥራ ይናገርም፤ ከጥንት የፈጠርሁትን ሕዝብ ያዘጋጅልኝ፥ የሚመጣውም ነገር ሳይደርስ ይንገሩኝ።
8 ፤ አትፍሩ አትደንግጡም፤ ከጥንቱ ጀምሬ አልነገርኋችሁምን? ወይስ አላሳየኋችሁምን? እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ። ከእኔ ሌላ አምላክ አለን? አምባ የለም፤ ማንንም አላውቅም።
9 ፤ የተቀረጸውን ምስል የሚሠሩ ሁሉ ከንቱዎች ናቸው፥ የወደዱትም ነገር አይረባቸውም፤ ምስክሮቻቸውም አያዩምና አያውቁም፤ ስለዚህ ያፍራሉ።
10 ፤ አምላክን የሠራ ወይስ ለምንም የማይረባ ምስልን የቀረጸ ማን ነው?
11 ፤ እነሆ፥ ባልንጀሮቹ ሁሉ ያፍራሉ፥ ሠራተኞቹም ከሰዎች ወገን ናቸው፤ ሁላቸው ተሰብስበው ይቁሙ፤ ይፈራሉ በአንድነትም ያፍራሉ።
12 ፤ ብረት ሠሪ መጥረቢያውን ይሠራል፥ በፍምም ውስጥ ያደርገዋል፥ በመዶሻም መትቶ ቅርጽ ይሰጠዋል፥ በክንዱም ኃይል ይሠራዋል፥ እርሱም ይራባል ይደክምማል፥ ውኃም አይጠጣም ይታክትማል።
13 ፤ ጠራቢውም ገመድ ይዘረጋል በበረቅም ያመለክተዋል በመቅረጫም ይቀርጸዋል በመለኪያም ይለካዋል፤ በቤትም ውስጥ ይቀመጥ ዘንድ በሰው አምሳልና በሰው ውበት ያስመስለዋል።
14 ፤ የዝግባን ዛፎች ይቈርጣል፤ የዞጲንና የኮምቦልን ዛፍ ይመርጣል፥ ከዱር ዛፎችም መካከል ይጠነክር ዘንድ ይተወዋል፤ የጥድንም ዛፍ ይተክላል ዝናብም ያበቅለዋል።
15 ፤ ለሰውም ማገዶ ይሆናል፤ ከእርሱም ወስዶ ይሞቃል፥ አንድዶም እንጀራ ይጋግርበታል፤ ከእርሱም አምላክ አበጅቶ ይሰግድለታል፥ የተቀረጸውንም ምስል ሠርቶ በእርሱ ፊት ይንበረከካል።
16 ፤ ግማሹን በእሳት ያቃጥላል፥ በዚያ በግማሹ ሥጋ ይበላል፥ ሥጋም ይጠብስበትና ይጠግባል፤ ይሞቃልና። እሰይ ሞቅሁ፥ እሳቱን አይቻለሁ ይላል።
17 ፤ የቀረውንም እንጨት አምላክ አድርጎ ምስል ይቀርጽበታል፤ በፊቱም ተጐንብሶ ይሰግዳል ወደ እርሱም እየጸለየ። አምላኬ ነህና አድነኝ ይላል።
18 ፤ አያውቁም፥ አያስቡም፤ እንዳያዩ ዓይኖቻቸውን፥ እንዳያስተውሉ ልቦቻቸውን ጨፍነዋል።
19 ፤ በልቡም ማንም አያስብም። ግማሽዋን በእሳት አቃጥያለሁ፥ በፍምዋም ላይ እንጀራን ጋግሬአለሁ፥ ሥጋም ጠብሼ በልቻለሁ፤ የቀረውንም አስጸያፊ ነገር አደርጋለሁን? ለዛፍስ ግንድ እሰግዳለሁን? እንዲልም እውቀትና ማስተዋል የለውም።
20 ፤ አመድ ይበላል፥ የተታለለ ልብ አስቶታል፥ ነፍሱን ለማዳን አይችልም፥ ወይም። በቀኝ እጄ ሐሰት አለ አይልም።
21 ፤ ያዕቆብ ሆይ፥ አንተም እስራኤል፥ ባሪያዬ ነህና ይህን አስብ፤ እኔ ሠርቼሃለሁ አንተም ባሪያዬ ነህ፤ እስራኤል ሆይ፥ በእኔ ዘንድ ያልተረሳ ትሆናለህ።
22 ፤ መተላለፍህን እንደ ደመና፥ ኃጢአትህንም እንደ ጭጋግ ደምስሼአለሁ፤ ተቤዥቼሃለሁና ወደ እኔ ተመለስ።
23 ፤ ሰማያት ሆይ፥ እግዚአብሔር አድርጎታልና ዘምሩ፤ እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቶአልና፥ በእስራኤልም ዘንድ ይከበራልና አንተ የምድር ጥልቅ ሆይ፥ ጩኽ፤ እናንተም ተራሮች አንተም ዱር በአንተም ያለ ዛፍ ሁሉ፥ እልል በሉ።
24 ፤ ከማኅፀን የሠራህ፥ የሚቤዥህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ። ሁሉን የፈጠርሁ፥ ሰማያትን ለብቻዬ የዘረጋሁ ምድርንም ያጸናሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ ከእኔ ጋር ማን ነበረ?
25 ፤ የሐሰተኞችን ምልክት ከንቱ አደርጋለሁ፥ ምዋርተኞችንም አሳብዳለሁ፥ ጥበበኞቹንም ወደ ኋላ እመልሳለሁ እውቀታቸውንም ስንፍና አደርጋለሁ፤
26 ፤ የባሪያዬን ቃል አጸናለሁ፥ የመልእክተኞቼንም ምክር እፈጽማለሁ፤ ኢየሩሳሌምን። የሰው መኖሪያ ትሆኛለሽ፥ የይሁዳንም ከተሞች። ትታነጻላችሁ ፍራሾቻችሁንም አቆማለሁ እላለሁ፤
27 ፤ ቀላዩንም። ደረቅ ሁን፥ ፈሳሾችህንም አደርቃለሁ እላለሁ፤
28 ፤ ቂሮስንም። እርሱ እረኛዬ ነው፤ እርሱም ኢየሩሳሌምን ። ትታነጺያለሽ ቤተ መቅደስም ይመሠረታል ብሎ ፈቃዴን ሁሉ ይፈጽማል እላለሁ።