ምዕራፍ 25

አቤቱ፥ አንተ አምላኬ ነህ፤ ድንቅን ነገር የዱሮ ምክርን በታማኝነትና በእውነት አድርገሃልና ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ ስምህንም አመሰግናለሁ።
2 ፤ ከተማይቱን የድንጋይ ክምር፥ የተመሸገችውን ከተማ ውድማ እንድትሆን፥ የኀጥአንንም አዳራሽ ከተማ እንዳትሆን አድርገሃል፤ ከቶ አትሠራም።
3 ፤ ስለዚህ ኃያላኑ ወገኖች ያከብሩሃል፥ የጨካኞች አሕዛብ ከተማም ትፈራሃለች።
4 ፤ የጨካኞችም ቍጣ እስትንፋስ ቅጥርን እንደሚመታ ዐውሎ ነፋስ በሆነ ጊዜ፥ ለድሀው መጠጊያ፥ ለችግረኛው በጭንቁ ጊዜ መጠጊያ፥ ከውሽንፍር መሸሸጊያ ከሙቀትም ጥላ ሆነሃል።
5 ፤ እንደ ሙቀት በደረቅ ስፍራ የኀጥአንን ጩኸት ዝም ታሰኛለህ፤ ሙቀትም በደመና ጥላ እንዲበርድ እንዲሁ የጨካኞች ዝማሬ ይዋረዳል።
6 ፤ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝብ ሁሉ በዚህ ተራራ ላይ ታላቅ የሰባ ግብዣ፥ ያረጀ የወይን ጠጅ፥ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፥ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል።
7 ፤ በዚህም ተራራ ላይ በወገኖች ሁሉ ላይ የተጣለውን መጋረጃ፥ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋውን መሸፈኛ ያጠፋል።
8 ፤ ሞትን ለዘላለም ይውጣል፥ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፥ የሕዝቡን ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።
9 ፤ በዚያም ቀን። እነሆ፥ አምላካችን ይህ ነው፤ ተስፋ አድርገነዋል፥ ያድነንማል፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ ጠብቀነዋል፤ በማዳኑ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን ይባላል።
10 ፤ የእግዚአብሔርም እጅ በዚህ ተራራ ላይ ታርፋለች፥ ጭድም በጭቃ ውስጥ እንደሚረገጥ እንዲሁ ሞዓብ በስፍራው ይረገጣል።
11 ፤ ዋናተኛም ሲዋኝ እጁን እንደሚዘረጋ፥ እንዲሁ በመካከሉ እጁን ይዘረጋል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ትዕቢቱን ከእጁ ተንኰል ጋር ያዋርዳል።
12 ፤ የተመሸገውንም ከፍ ከፍ ያለውንም ቅጥርህን ዝቅ ያደርገዋል፥ ያዋርደውማል፥ ወደ መሬትም እስከ አፈር ድረስ ይጥለዋል።