ምዕራፍ 31

ስለ እርዳታ ወደ ግብጽ ለሚወርዱ በፈረሶችም ለሚደገፉ፥ ስለ ብዛታቸውም በሰረገሎች፥ እጅግ ብርቱዎችም ስለ ሆኑ በፈረሰኞች ለሚታመኑ፥ ወደ እስራኤልም ቅዱስ ለማይመለከቱ እግዚአብሔርንም ለማይፈልጉ ወዮላቸው!
2 ፤ እርሱ ግን ደግሞ ጠቢብ ነው፥ ክፉንም ነገር ያመጣል፥ ቃሉንም አይመልስም፥ በክፉም አድራጊዎች ቤት ላይ በደልንም በሚሠሩ ረዳት ላይ ይነሣል።
3 ፤ ግብጻውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፥ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፤ እግዚአብሔርም እጁን በዘረጋ ጊዜ፥ ረጂው ይሰናከላል ተረጂውም ይወድቃል፥ ሁሉም በአንድ ላይ ይጠፋሉ።
4 ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ይለኛልና። አንበሳ ወይም የአንበሳ ደቦል በንጥቂያው ላይ ሲያገሳ፥ ብዙ እረኞች ቢከማቹበት ከቃላቸው እንደማይፈራ ከድምፃቸውም እንደማይዋረድ፥ እንዲሁ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በጽዮን ተራራና በኮረብታዋ ላይ ይዋጋ ዘንድ ይወርዳል።
5 ፤ እንደሚበርር ወፍ እንዲሁ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ይጋርዳታል፤ ይከልላታል፥ ይታደጋታል፥ አልፎም ያድናታል።
6 ፤ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ አጥብቃችሁ ወደ ዐመፃችሁበት ተመለሱ።
7 ፤ በዚያም ቀን እያንዳንዳቸው እጆቻቸው ለኃጢአት የሠሩላቸውን የብሩንና የወርቁን ጣዖቶቻቸውን ይጥላሉ።
8 ፤ አሦርም የሰው ባልሆነ ሰይፍ ይወድቃል፥ የሰውም ያልሆነ ሰይፍ ይበላዋል፤ ከሰይፍም ይሸሻሉ ጐበዛዝቱም ገባሮች ይሆናሉ።
9 ፤ አምባው ከፍርሃት የተነሣ ያልፋል መሳፍንቱም ከዓላማው የተነሣ ይደነግጣሉ፥ ይላል እሳቱ በጽዮን እቶኑም በኢየሩሳሌም የሆነ እግዚአብሔር።