ምዕራፍ 46

ቤል ተዋረደ፥ ናባው ተሰባበረ፤ ጣዖቶቻቸው በእንስሳና በከብት ላይ ተጭነዋል፤ ሸክሞቻችሁ ለደካማ እንስሳ ከባድ ጭነት ሆነዋል።
2 ፤ ተጐነበሱ በአንድነትም ተዋረዱ፤ ሸክሙን ለማዳን አልቻሉም፥ ራሳቸው ግን ተማረኩ።
3 ፤ እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ የእስራኤልም ቤት ቅሬታ ሁሉ፥ ከሆድ ያነሣኋችሁ ከማኅፀንም የተሸከምኋችሁ፥ ስሙኝ።
4 ፤ እስከ ሽምግልና ድረስ እኔ ነኝ፥ እስከ ሽበትም ድረስ እሸከማችኋለሁ፤ እኔ ሠርቻለሁ እኔም አነሣለሁ፤ እኔ እሸከማለሁ እኔም አድናለሁ።
5 ፤ በማን ትመስሉኛላችሁ? ከማንስ ጋር ታስተካክሉኛላችሁ? እንመሳሰል ዘንድ ከማን ጋር ታስተያዩኛላችሁ?
6 ፤ ወርቁን ከኮረጆ የሚያፈስሱ ብሩንም በሚዛን የሚመዝኑ እነርሱ አንጥረኛውን ይቀጥራሉ፥ እርሱም አምላክ አድርጎ ይሠራ ዋል፤ ለዚያም ይጐነበሱለታል ይሰግዱለትማል።
7 ፤ በጫንቃቸው ላይ አንሥተው ይሸከሙታል በስፍራውም ያደርጉታል፥ በዚያም ይቆማል፥ ከስፍራውም ፈቀቅ አይልም፤ ሰውም ወደ እርሱ ቢጮኽ አይሰማውም ከመከራውም አያድነውም።
8 ፤ ይህን አስቡና አልቅሱ፤ ተላላፊዎች ሆይ፥ ንስሐ ግቡ፥ ልባችሁንም መልሱ።
9 ፤ እኔ አምላክ ነኝና፥ ሌላም የለምና የቀድሞውን የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም።
10 ፤ በመጀመሪያ መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ እፈጽማለሁ እላለሁ።
11 ፤ ከምሥራቅ ነጣቂ ወፍን፥ ከሩቅም አገር ምክሬን የሚያደርገውን ሰው እጠራዋለሁ። ተናግሬአለሁ፤ እፈጽማለሁ፤ አስቤአለሁ አደርግማለሁ።
12 ፤ እናንተ ከጽድቅ የራቃችሁ እልከኞች፥ ስሙኝ፤
13 ፤ ጽድቄን አቀርባለሁ፥ አይርቅም መድኃኒቴም አይዘገይም፤ ከጽዮን ለክብር እንዲሆን መድኃኒትን ለእስራኤል ሰጥቻለሁ።