ምዕራፍ 51

እናንተ ጽድቅን የምትከተሉ እግዚአብሔርንም የምትሹ፥ ስሙኝ፤ ከእርሱ የተቈረጣችሁበትን ድንጋይ ከእርሱም የተቈፈራችሁበትን ጕድጓድ ተመልከቱ።
2 ፤ ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም፥ ወደ ወለደቻችሁም ወደ ሳራ ተመልከቱ፤ አንድ ብቻውን በሆነ ጊዜ ጠራሁት፥ ባረክሁትም አበዛሁትም።
3 ፤ እግዚአብሔርም ጽዮንን ያጽናናል፤ በእርስዋም ባድማ የሆነውን ሁሉ ያጽናናል፥ ምድረ በዳዋንም እንደ ዔደን በረሀዋንም እንደ እግዚአብሔር ገነት ያደርጋል፤ ደስታና ተድላ ምስጋናና የዝማሬ ድምፅ ይገኝበታል።
4 ፤ ወገኔ ሆይ፥ አድምጠኝ፤ ሕዝቤ ሆይ፥ ስማኝ፤ ሕግ ከእኔ ይወጣልና ፍርዴም ለአሕዛብ ብርሃን ይሆናልና።
5 ፤ ጽድቄ ፈጥኖ ቀርቦአል፥ ማዳኔም ወጥቶአል፥ ክንዴም በአሕዛብ ላይ ይፈርዳል፤ ደሴቶች እኔን በመተማመን ይጠባበቃሉ፥ በክንዴም ይታመናሉ።
6 ፤ ዓይናችሁን ወደ ሰማይ አንሡ፥ ወደ ታችም ወደ ምድር ተመልከቱ፤ ሰማያት እንደ ጢስ በንነው ይጠፋሉ፥ ምድርም እንደ ልብስ ታረጃለች፥ የሚኖሩባትም እንዲሁ ይሞታሉ፤ ማዳኔ ግን ለዘላለም ይሆናል፥ ጽድቄም አይፈርስም።
7 ፤ ጽድቅን የምታውቁ ሕጌም በልባችሁ ያለ ሕዝብ ሆይ፥ ስሙኝ፤ የሰውን ተግዳሮት አትፍሩ፥ በስድባቸውም አትደንግጡ።
8 ፤ እንደ ልብስም ብል ይበላቸዋል፥ እንደ በግ ጠጕርም ትል ይበላቸዋል፤ ጽድቄ ግን ለዘላለም ማዳኔም ለትውልድ ሁሉ ይሆናል።
9 ፤ የእግዚአብሔር ክንድ ሆይ፥ ተነሥ፥ ተነሥ፥ ኃይልንም ልበስ፤ በቀድሞው ወራትና በጥንቱ ዘመን በነበረው ትውልድ እንደ ሆነው ተነሥ። ረዓብን የቈራረጥህ ዘንዶውንም የወጋህ አንተ አይደለህምን?
10 ፤ ባሕሩንና የታላቁን ጥልቅ ውኃ ያደረቅኸው፥ የዳኑትም ይሻገሩ ዘንድ ጠሊቁን ባሕር መንገድ ያደረግህ አንተ አይደለህምን?
11 ፤ እግዚአብሔርም የተቤዣቸው ይመለሳሉ ወደ ጽዮንም ይመጣሉ፤ የዘላለምም ደስታ በራሳቸው ላይ ይሆናል፤ ደስታንና ተድላን ያገኛሉ፥ ኀዘንና ልቅሶም ይሸሻል።
12 ፤ የማጽናናችሁ እኔ ነኝ፥ እኔ ነኝ፤ የሚሞተውን ሰው እንደ ሣርም የሚጠወልገውን የሰው ልጅ ትፈራ ዘንድ አንተ ማን ነህ?
13 ፤ ሰማያትንም የዘረጋው ምድርንም የመሠረተውን ፈጣሪህን እግዚአብሔርን ረስተሃል፤ ያጠፋ ዘንድ ባዘጋጀ ጊዜ ከአስጨናቂው ቍጣ የተነሣ ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ፈርተሃል፤ የአስጨናቂው ቍጣ የት አለ?
14 ፤ ምርኮኛ ፈጥኖ ይፈታል፤ አይሞትም ወደ ጕድጓድም አይወርድም፥ እንጀራም አይጐድልበትም።
15 ፤ ሞገዱም እንዲተምም ባሕርን የማናውጥ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፥ ስሜም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።
16 ፤ ሰማያትን እዘረጋ ዘንድ ምድርንም እመሠርት ዘንድ፥ ጽዮንንም። አንቺ ሕዝቤ ነሽ እል ዘንድ ቃሌን በአፍህ አድርጌአለሁ፥ በእጄም ጥላ ጋርጄሃለሁ።
17 ፤ ከእግዚአብሔር እጅ የቍጣውን ጽዋ የጠጣሽ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ንቂ፥ ንቂ፥ ቁሚ፤ የሚያንገደግድን ዋንጫ ጠጥተሻል ጨልጠሽውማል።
18 ፤ ከወለደቻቸው ልጆች ሁሉ የሚመራት የለም፥ ካሳደገቻቸውም ልጆች ሁሉ እጅዋን የሚይዝ የለም።
19 ፤ እነዚህ ሁለት ነገሮች ሆነውብሻል፥ ማንስ ያስተዛዝንሻል? መፈታትና ጥፋት ራብና ሰይፍ ናቸው፤ እንዴትስ አድርጌ አጽናናሻለሁ?
20 ፤ ልጆችሽ ዝለዋል፤ በወጥመድ እንደተያዘ ሚዳቋ በአደባባይ ሁሉ ራስ ላይ ተኝተዋል፤ በእግዚአብሔር ቍጣና በአምላክሽ ተግሣጽ ተሞልተዋል።
21 ፤ ስለዚህም ያለ ወይን ጠጅ የሰከርሽ አንቺ ችግረኛ፥ ይህን ስሚ፤
22 ፤ ስለ ወገኑ የሚምዋገት አምላክሽ ጌታሽ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የሚያንገደግድን ጽዋ የቍጣዬንም ዋንጫ ከእጅሽ ወስጃለሁ፤ ደግመሽም ከእንግዲህ ወዲህ አትጠጪውም።
23 ፤ ነፍስሽንም። እንሻገር ዘንድ ዝቅ በዪ በሚሉአት በአስጨናቂዎችሽ እጅ አኖረዋለሁ፤ ጀርባሽንም ለሚሻገሩት እንደ መሬትና እንደ መንገድ አደረግሽላቸው።