ምዕራፍ 47

አንቺ ድንግል የባቢሎን ልጅ ሆይ፥ ውረጂ በትቢያም ላይ ተቀመጪ፤ የከለዳውያን ሴት ልጅ ሆይ፥ ከዚህ በኋላ ቅልጣናምና ቅምጥል አትባይምና ያለ ዙፋን በመሬት ላይ ተቀመጪ።
2 ፤ ወፍጮ ወስደሽ ዱቄትን ፍጪ፤ መሸፈኛሽን አውጪ ረጅሙንም ልብስሽን አውልቀሽ ጣዪው፤ ባትሽን ግለጪ፥ ወንዙን ተሻገሪ።
3 ፤ ኀፍረተ ሥጋሽ ይገለጣል እፍረትሽም ይታያል፤ እኔ እበቀላለሁ፥ ለማንም አልራራም።
4 ፤ ታዳጊያችን፥ ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ የእስራኤል ቅዱስ ነው።
5 ፤ የከለዳውያን ሴት ልጅ ሆይ፥ ከዚህ በኋላ። የመንግሥታት እመቤት አትባይምና ዝም ብለሽ ተቀመጪ ወደ ጨለማም ውስጥ ግቢ።
6 ፤ በሕዝቤ ላይ ተቈጥቼ ነበር ርስቴንም አረከስሁ በእጅሽም አሳልፌ ሰጠኋቸው፤ ከእነርሱ ጋር ምሕረት አላደረግሽም፥ በሽማግሌዎቻቸው ላይ ቀንበርሽን እጅግ አክብደሻል።
7 ፤ አንቺም። እኔ ለዘላለም እመቤት እሆናለሁ ብለሻል፤ ይህንም በልብሽ አላደረግሽም ፍጻሜውንም አላሰብሽም።
8 ፤ አሁንም አንቺ ቅምጥል ተዘልለሽ የምትቀመጪ፥ በልብሽም። እኔ ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም፤ መበለትም ሆኜ አልኖርም የወላድ መካንነትንም አላውቅም የምትዪ ይህን ስሚ፤
9 ፤ አሁን ግን በአንድ ቀን እነዚህ ሁለት ነገሮች፥ የወላድ መካንነትና መበለትነት፥ በድንገት ይመጡብሻል፤ ስለ መተቶችሽ ብዛትና ስለ አስማቶችሽ ጽናት ፈጽመው ይመጡብሻል።
10 ፤ በክፋትሽ ታምነሻል፤ የሚያየኝ የለም ብለሻል፤ ጥበብሽና እውቀትሽ አታልለውሻል፥ በልብሽም። እኔ ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም ብለሻል።
11 ፤ ስለዚህ ምክንያት ክፉ ነገር ይመጣብሻል፥ በምዋርትሽም እንዴት እንደምታርቂው አታውቂም፤ ጉዳት ይውድቅብሻል ታስወግጅውም ዘንድ አይቻልሽም፤ የማትውቂያትም ጕስቍልና ድንገት ትመጣብሻለች።
12 ፤ ምናልባትም መጠቀም ትችዪ ወይም ታስደነግጪ እንደ ሆነ፥ ከአስማቶችሽና ከሕፃንነትሽ ጀምረሽ ከደከምሽበት ከመተቶችሽ ብዛት ጋር ቁሚ።
13 ፤ በምክርሽ ብዛት ደክመሻል፤ አሁንም የሰማይን ከዋክብት የሚቈጥሩ፥ ከዋክብትንም የሚመለከቱ፥ በየመባቻውም የሚመጣውን ነገር የሚናገሩ ተነሥተው ከሚመጣብሽ ነገር ያድኑሽ።
14 ፤ እነሆ፥ እንደ እብቅ ይሆናሉ፥ እሳትም ያቃጥላቸዋል ሰውነታቸውንም ከነበልባል ኃይል አያድኑም፤ እርሱም ሰው እንደሚሞቀው ፍም፥ ወይም በፊቱ ሰው እንደሚቀመጥበት እሳት ያለ አይደለም።
15 ፤ የደከምሽባቸው ነገሮች እንዲህ ይሆኑብሻል፤ ከሕፃንነትሽ ጀምረው ከአንቺ ጋር ይነግዱ የነበሩ እያንዳንዳቸው ወደ ስፍራቸው ይሄዳሉ፥ የሚያድንሽም የለም።