ትንቢተ ኢሳይያስ
ምዕራፍ 17
ስለ ደማስቆ የተነገረ ሸክም። እነሆ፥ ደማስቆ ከተማ ከመሆን ተቋርጣለች፤ ባድማና የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች።
2 ፤ ከተሞችዋ ለዘላለም የተፈቱ ይሆናሉ፤ ለመንጋ ማሰማሪያ ሆናሉ፤ መንጎች በዚያ ያርፋሉ የሚያስፈራቸውም የለም።
3 ፤ ምሽግም ከኤፍሬም፥ መንግሥትም ከደማስቆ ተወገደች፤ የሶርያም ቅሬታ እንደ እስራኤል ልጆች ክብር ይሆናል ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።
4 ፤ በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ የያዕቆብ ክብር ይደክማል የሥጋውም ውፍረት ይከሳል።
5 ፤ አጫጅ የቆመውን እህል በእጁ ሰብስቦ ዛላውን እንደሚያጭድ ይሆናል፤ በራፋይም ሸለቆ ቃርሚያ እንደሚለቅም እንዲሁ ይሆናል።
6 ፤ ወይራ በተመታ ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት ፍሬ በራሱ ላይ እንደሚቀር፥ አራት ወይም አምስት በዛፊቱ ጫፍ እንደሚገኝ፥ በእርሱ ዘንድ ቃርሚያ ይቀራል ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር።
7 ፤ በዚያ ቀን ሰው ወደ ፈጣሪው ይመለከታል፥ ዓይኖቹም ወደ እስራኤል ቅዱስ ያያሉ።
8 ፤ እጁም የሠራችውን መሠዊያ አይመለከትም፤ ጣቶቹም ወደ አበጁአቸው፥ ወደ ማምለኪያ ዐፀዶች ወይም ወደ ፀሐይ ምስሎች፥ አያይም።
9 ፤ በዚያም ቀን በእስራኤል ልጆች ፊት የአሞራውያንና የኤውያውያን ከተሞች እንደ ተፈቱ፥ እንዲሁ ከተሞችህ ይፈታሉ፥ ባድማም ይሆናሉ።
10 ፤ የደኅንነትህን አምላክ ረስተሃል፥ የረድኤትህንም ጌታ አላሰብህም፤ ስለዚህ ያማረውን ተክል ተክለሃል፥ እንግዳንም ዘር ዘርተሃል።
11 ፤ በተከልህበት ቀን ታበቅለዋለህ፥ በነጋውም ዘርህን እንዲያብብ ታደርገዋለህ፤ ነገር ግን በኀዘንና በትካዜ ቀን መከሩ ይሸሻል።
12 ፤ እንደ ባሕር ሞገድ ድምፅ ለሚተምሙ ለወገኖች ብዛት፥ እንደ ኃይለኛም ውኃ ጩኸት ለሚጮኹ አሕዛብ ወዮላቸው!
13 ፤ አሕዛብ እንደ ብዙ ውኃ ጩኸት ይጮኻሉ፤ እርሱ ግን ይገሥጻቸዋል፥ እነርሱም እየሸሹ ይርቃሉ፥ በተራራም ላይ እንዳለ እብቅ በነፋስ ፊት፥ ዐውሎ ነፋስ እንደሚያዞረው ትቢያ ይበተናሉ።
14 ፤ በመሸ ጊዜ፥ እነሆ፥ ድንጋጤ አለ፤ ከማለዳም በፊት አይገኙም። የዘረፉን ሰዎች እድል ፈንታ፥ የበዘበዙን ዕጣ ይህ ነው።