ምዕራፍ 2

የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ቃል።
2 ፤ በዘመኑም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፥ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበሰባሉ።
3 ፤ ሕግ ከጽዮን የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው። ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ በጎዳናውም እንሄዳለን ይላሉ።
4 ፤ በአሕዛብም መካከል ይፈርዳል፥ በብዙ አሕዛብም ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፥ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።
5 ፤ እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ ኑ፥ በእግዚአብሔር ብርሃን እንሂድ።
6 ፤ ሕዝብህን የያዕቆብን ቤት ትተሃልና፤ ይኸውም የምሥራቅን ሰዎች አመል ስለ ተሞሉ፥ እንደ ፍልስጥኤማውያንም ምዋርተኞች ስለ ሆኑ፥ ከባዕድ ልጆችም ጋር ስለ ተባበሩ ነው።
7 ፤ ምድራቸው በብርና በወርቅ ተሞልታለች፥ ለመዛግብቶቻቸውም ፍጻሜ የለውም፤ ምድራቸውም ደግሞ በፈረሶች ተሞልታለች፥ ለሠረገሎቻቸውም ፍጻሜ የለውም።
8 ፤ ምድራቸው ደግሞ በጣዖታት ተሞልታለች፤ ጣቶቻቸውም ላደረጉት ለእጃቸው ሥራ ይሰግዳሉ።
9 ፤ ታናሹም ሰው ዝቅ ብሎአል፥ ጨዋውም ተዋርዶአል፤ ኃጢአታቸውንም ይቅር አትበላቸው።
10 ፤ ከእግዚአብሔር ማስደንገጥና ከግርማው ክብር የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻ ግባ፥ በመሬትም ውስጥ ተሸሸግ።
11 ፤ ከፍ ያለችውም የሰው ዓይን ትዋረዳለች፥ የሰዎችም ኵራት ትወድቃለች፥ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ብቻውን ከፍ ከፍ ይላል።
12 ፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቀን በትዕቢተኛውና በኵራተኛው ሁሉ ላይ ከፍ ባለውም ላይ ይሆናል፥ እርሱም ይዋረዳል፤
13 ፤ ደግሞም በረጅሙ ከፍ ባለው በሊባኖስ ዝግባ ሁሉ ላይ፥ በባሳንም ዛፍ ሁሉ ላይ፥
14 ፤ በረጅሙም ተራራ ሁሉ ላይ፥ ከፍ ባለውም ኮረብታ ሁሉ ላይ፥
15 ፤ በረጅሙም ግንብ ሁሉ ላይ፥ በተመሸገውም ቅጥር ሁሉ ላይ፥
16 ፤ በተርሴስም መርከብ ሁሉ ላይ፥ በሚያማምሩ ጣዖታትም ሁሉ ላይ ይሆናል።
17 ፤ ሰውም ሁሉ ይዋረዳል፥ የሰውም ኵራት ይወድቃል፥ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ብቻ ከፍ ከፍ ይላል።
18 ፤ ጣዖቶቻቸውም ሁሉ ፈጽመው ይጠፋሉ።
19 ፤ እግዚአብሔርም ምድርን ያናውጥ ዘንድ በተነሣ ጊዜ ሰዎች ከማስደንገጡና ከግርማው ክብሩ የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻና ወደ ምድር ንቃቃት ውስጥ ይገባሉ።
20 ፤ በዚያን ቀን ሰው ይሰግድላቸው ዘንድ ያበጁአቸውን የብሩንና የወርቁን ጣዖቶቹን ለፍልፈልና ለሌሊት ወፍ ይጥላል።
21 ፤ እግዚአብሔርም ምድርን ያናውጥ ዘንድ በተነሣ ጊዜ ከማስደንገጡና ከግርማው ክብር የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻና ወደ ተሰነጠቁ ዓለቶች ውስጥ ይገባሉ።
22 ፤ እስትንፋሱ በአፍንጫው ውስጥ ያለበትን ሰው ተዉት፤ እርሱ ስለ ምን ይቈጠራል?