ምዕራፍ 40

አጽናኑ፥ ሕዝቤን አጽናኑ ይላል አምላካችሁ።
2 ፤ ለኢየሩሳሌም ልብ ተናገሩ የተቀጠረችበት ወራት እንደ ተፈጸመ፥ ኃጢአትዋም እንደ ተሰረየ፥ ከእግዚአብሔርም እጅ ስለ ኃጢአትዋ ሁሉ ሁለት እጥፍ እንደ ተቀበለች ወደ እርስዋ ጩኹ።
3 ፤ የአዋጅ ነጋሪ ቃል። የእግዚአብሔርን መንገድ በምድረ በዳ ጥረጉ፥ ለአምላካችንም ጐዳና በበረሀ አስተካከሉ።
4 ፤ ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፥ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማውም ይቃናል፥ ስርጓጕጡም ሜዳ ይሆናል፤
5 ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ በአንድነት ያየዋል፥ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሮአልና።
6 ፤ ጩኽ የሚል ሰው ቃል፤ ምን ብዬ ልጩኽ? አልሁ። ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው፥ ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው።
7 ፤ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ይነፍስበታልና ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፤ በእውነት ሕዝቡ ሣር ነው።
8 ፤ ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፥ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።
9 ፤ የምስራች የምትነግሪ ጽዮን ሆይ፥ ከፍ ወዳለው ተራራ ውጪ የምስራች የምትነግሪ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ድምፅሽን በኃይል አንሺ፤ አንሺ፥ አትፍሪ፤ ለይሁዳም ከተሞች። እነሆ፥ አምላካችሁ! ብለሽ ንገሪ።
10 ፤ እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይመጣል ክንዱም ስለ እርሱ ይገዛል፤ እነሆ፥ ዋጋው ከእርሱ ጋር ደመወዙም በፊቱ ነው።
11 ፤ መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፥ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፥ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል።
12 ፤ ውኆችን በእፍኙ የሰፈረ፥ ሰማይንም በስንዝር የለካ፥ የምድርንም አፈር በመስፈሪያ ሰብስቦ የያዘ፥ ተራሮችን በሚዛን ኮረብቶችንም በሚዛኖች የመዘነ ማን ነው?
13 ፤ የእግዚአብሔርን መንፈስ ያዘዘ፥ ወይስ አማካሪ ሆኖ ያስተማረው ማን ነው?
14 ፤ ወይስ ከማን ጋር ተመካከረ? ወይስ ማን መከረው? የፍርድንም መንገድ ማን አስተማረው? እውቀትንስ ማን አስተማረው? የማስተዋልንስ መንገድ ማን አሳየው?
15 ፤ እነሆ፥ አሕዛብ በገንቦ እንዳለች ጠብታ ናቸው፥ በሚዛንም እንዳለ ትንሽ ትቢያ ተቈጥረዋል፤ እነሆ፥ ደሴቶችን እንደ ቀላል ነገር ያነሣል።
16 ፤ ሊባኖስ ለማንደጃ እንስሶችዋም ለሚቃጠል መሥዋዕት አይበቁም።
17 ፤ አሕዛብ ሁሉ በፊቱ እንዳልነበሩ ናቸው፤ ከምናምን እንደሚያንሱ፥ እንደ ከንቱ ነገርም ይቈጥራቸዋል።
18 ፤ እንግዲህ እግዚአብሔርን በማን ትመስሉታላችሁ? ወይስ በምን ምሳሌ ታስተያዩታላችሁ?
19 ፤ የተቀረጸውንስ ምስል ሠራተኛ ሠርቶታል፥ አንጥረኛም በወርቅ ለብጦታል፥ የብሩንም ሰንሰለት አፍስሶለታል።
20 ፤ ለዚህ መባዕ ገንዘቡ ያልበቃው ድሀ የማይነቅዘውን እንጨት ይመርጣል፤ ምስሉም እንዳይናወጥ ያቆመው ዘንድ ብልህ ሠራተኛን ይፈልጋል።
21 ፤ አላወቃችሁምን? ወይስ አልሰማችሁምን? ከጥንትስ አልተወራላችሁምን? ወይስ ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁምን?
22 ፤ እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀምጣል፥ በእርስዋም የሚኖሩት እንደ አንበጣ ናቸው፤ ሰማያትን እንደ መጋረጃ የሚዘረጋቸው እንደ ድንኳንም ለመኖርያ የሚዘረጋቸው፥
23 ፤ አለቆችንም እንዳልነበሩ፥ የምድርንም ፈራጆች እንደ ከንቱ ነገር የሚያደርጋቸው እርሱ ነው።
24 ፤ ገና እንደ ተተከሉና እንደ ተዘሩ፥ በምድርም ሥር ገና እንደ ሰደዱ ወዲያውኑ ነፈሰባቸው፥ እነርሱም ደረቁ፥ ዐውሎ ነፋስም እንደ እብቅ ጠረጋቸው።
25 ፤ እንግዲህ እተካከለው ዘንድ በማን መሰላችሁኝ? ይላል ቅዱሱ።
26 ፤ ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው? ሠራዊታቸውን በቍጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፥ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም።
27 ፤ ያዕቆብ ሆይ፥ እስራኤልም ሆይ። መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች ፍርዴም ከአምላኬ አልፋለች ለምን ትላለህ? ለምንስ እንዲህ ትናገራለህ?
28 ፤ አላወቅህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፥ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ ነው፤ አይደክምም፥ አይታክትም፥ ማስተዋሉም አይመረመርም።
29 ፤ ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፥ ጕልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል።
30 ፤ ብላቴኖች ይደክማሉ ይታክቱማል፥ ጐበዛዝቱም ፈጽሞ ይወድቃሉ፤
31 ፤ እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፥ አይደክሙም።