ምዕራፍ 41

ደሴቶች ሆይ፥ በፊቴ ዝም በሉ፤ አሕዛብም ኃይላቸውን ያድሱ፤ ይቅረቡም በዚያን ጊዜም ይናገሩ፤ ለፍርድ ለአንድነት እንቅረብ።
2 ፤ ከምሥራቅ አንዱን ያስነሣ በጽድቅም ወደ እግሩ የተጠራው ማን ነው? አሕዛብንም አሳልፎ በፊቱ ሰጠው፥ ነገሥታትንም አስገዛለት፤ ለሰይፉ እንደ ትቢያ ለቀስቱም እንደ ተጠረገ እብቅ አድርጎ ሰጣቸው።
3 ፤ አሳደዳቸው፥ እግሮቹም አስቀድመው ባልሄዱባት መንገድ በደኅነት አለፈ።
4 ፤ ይህን የሠራና ያደረገ፥ ትውልድንም ከጥንት የጠራ ማን ነው? እኔ እግዚአብሔር፥ ፊተኛው በኋላኞችም ዘንድ የምኖር እኔ ነኝ።
5 ፤ ደሴቶች አይተው ፈሩ፥ የምድርም ዳርቾች ተንቀጠቀጡ፤ ቀረቡም ደረሱም።
6 ፤ ሁሉም እያንዳንዱ ባልንጀራውን ይረዳው ነበር፥ ወንድሙንም። አይዞህ ይለው ነበር።
7 ፤ አናጢውም አንጥረኛውን፥ በመዶሻም የሚያሳሳውን መስፍ መችውን አጽናና፥ ስለ ማጣበቅ ሥራውም። መልካም ነው አለ፤ እንዳይንቀሳቀስም በችንካር አጋጠመው።
8 ፤ ባሪያዬ እስራኤል፥ የመረጥሁህ ያዕቆብ፥ የወዳጄ የአብርሃም ዘር ሆይ፥
9 ፤ አንተ ከምድር ዳርቻ የያዝሁህ ከማዕዘንዋም የጠራሁህና። አንተ ባሪያዬ ነህ፥ መርጬሃለሁ አልጥልህም ያልሁህ ሆይ፥
10 ፤ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ እኔ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ፤ አበረታሃለሁ፥ እረዳህማለሁ፥ በጽድቄም ቀኝ ደግፌ እይዝሃለሁ።
11 ፤ እነሆ የሚቆጡህ ሁሉ ያፍራሉ፥ ይዋረዱማል፤ የሚከራከሩህም እንዳልነበሩ ይሆናሉ፥ ይጠፉማል።
12 ፤ የሚያጣሉህንም ትሻቸዋለህ አታገኛቸውምም፥ የሚዋጉህም እንዳልነበሩና እንደ ምናምን ይሆናሉ።
13 ፤ እኔ አምላክህ እግዚአብሔር። አትፍራ፥ እረዳሃለሁ ብዬ ቀኝህን እይዛለሁና።
14 ፤ አንተ ትል ያዕቆብ የእስራኤልም ሰዎች ሆይ፥ አትፍሩ፤ እረዳሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የሚቤዥህም የእስራኤል ቅዱስ ነው።
15 ፤ እነሆ፥ እንደ ተሳለች እንደ አዲስ ባለ ጥርስ ማሄጃ አድርጌሃለሁ፤ ተራሮችንም ታሄዳለህ ታደቅቃቸውማለህ፥ ኮረብቶችንም እንደ ገለባ ታደርጋቸዋለህ።
16 ፤ ታበጥራቸዋለህ፥ ነፋስም ይጠርጋቸዋል፥ ዐውሎ ነፋስም ይበትናቸዋል፤ አንተም በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፥ በእስራኤልም ቅዱስ ትመካለህ።
17 ፤ ድሆችና ምስኪኖችም ውኃ ይሻሉ አያገኙምም፥ ምላሳቸውም በጥማት ደርቋል፤ እኔ እግዚአብሔር እሰማቸዋለሁ፥ የእስራኤል አምላክ እኔ አልተዋቸውም።
18 ፤ በወናዎቹ ኮረብቶች ላይ ወንዞችን፥ በሸለቆችም መካከል ምንጮችን እከፍታለሁ፤ ምድረ በዳውን ለውኃ መቆሚያ፥ የጥማትንም ምድር ለውኃ መፍለቂያ አደርጋለሁ።
19
20 ፤ የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንደ ሠራች፥ የእስራኤልም ቅዱስ እንደ ፈጠረው ያዩ ዘንድ ያውቁም ዘንድ ያስቡም ዘንድ በአንድነትም ያስተውሉ ዘንድ፥ በምድረ በዳ ዝግባውንና ግራሩን ባርሰነቱንና የዘይቱን ዛፍ አበቅላለሁ፥ በበረሀውም ጥዱንና አስታውን ወይራውንም በአንድነት አኖራለሁ።
21 ፤ ክርክራችሁን አቅርቡ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ማስረጃችሁን አምጡ፥ ይላል የያዕቆብ ንጉሥ።
22 ፤ ያምጡ፥ የሚሆነውንም ይንገሩን፤ ልብም እናደርግ ዘንድ ፍጻሜአቸውንም እናውቅ ዘንድ፥ የቀደሙት ነገሮች ምን እንደ ሆኑ ተናገሩ፥ የሚመጡትንም አሳዩን።
23 ፤ አማልክትም መሆናችሁን እናውቅ ዘንድ በኋላ የሚመጡትን ተናገሩ፤ እንደነግጥም ዘንድ በአንድነትም እናይ ዘንድ መልካሙን ወይም ክፉውን አድርጉ።
24 ፤ እነሆ፥ እንዳልነበረ ናችሁ፥ ሥራችሁም ከንቱ ነው፤ የሚመርጣችሁም አስጻያፊ ነው።
25 ፤ አንዱን ከሰሜን አነሣሁ መጥቶአልም፤ አንዱም ከፀሐይ መውጫ ስሜን የሚጠራ ይመጣል፤ በጭቃ ላይ እንደሚመጣ ሰው አፈርም እንደሚረግጥ ሸክለኛ በአለቆች ላይ ይመጣል።
26 ፤ እናውቅ ዘንድ ከጥንት የተናገረው። እውነት ነው እንልም ዘንድ ቀድሞ የተናገረው ማን ነው? የሚናገር የለም፥ የሚገልጥም የለም፥ ቃላችሁንም የሚሰማ የለም።
27 ፤ በመጀመሪያ ለጽዮን። እነኋቸው እላለሁ፤ ለኢየሩሳሌምም የምስራች ነጋሪን እሰጣለሁ።
28 ፤ ብመለከት ማንም አልነበረም፤ ብጠይቃቸውም የሚመልስልኝ አማካሪ በመካከላቸው የለም።
29 ፤ እነሆ፥ እነርሱ ሁሉ ከንቱዎች ናቸው፥ ሥራቸውም ምንምን ናት፤ ቀልጠው የተሠሩት ምስሎቻቸውም ነፋስና ኢምንት ናቸው።