ምዕራፍ 9

እርሱም። እያንዳንዳቸው የሚያጠፋ መሣሪያን በእጃቸው ይዘው ከተማይቱን የሚቀሥፉ ይቅረቡ ብሎ በታላቅ ድምፅ በጆሮዬ ጮኸ።
2 ፤ እነሆም፥ እያንዳንዳቸው አጥፊውን መሣሪያ በእጃቸው ይዘው ስድስት ሰዎች ወደ ሰሜን ከሚመለከተው ከላይኛው በር መንገድ መጡ፤ በመካከላቸውም የበፍታ ልብስ የለበሰ የጸሐፊም ቀለም ቀንድ በወገቡ የያዘ አንድ ሰው ነበረ። እነርሱም ገብተው በናሱ መሠዊያ አጠገብ ቆሙ።
3 ፤ የእስራኤልም አምላክ ክብር በበላዩ ከነበረበት ኪሩብ ተነሥቶ ወደ ቤቱ መድረክ ሄዶ ነበር፤ በፍታም የለበሰውን የጸሐፊውንም ቀለም ቀንድ በወገቡ የያዘውን ሰው ጠራ።
4 ፤ እግዚአብሔርም። በከተማይቱ በኢየሩሳሌም መካከል እለፍ፥ በመካከልዋም ስለ ተሠራው ርኵሰት ሁሉ በሚያለቅሱና በሚተክዙ ሰዎች ግምባር ላይ ምልክት ጻፍ አለው።
5 ፤ እኔም እየሰማሁ ለሌሎቹ። እርሱን ተከትላችሁ በከተማይቱ መካከል እለፉ ግደሉም፤ ዓይናችሁ አይራራ አትዘኑም፤
6 ፤ ሽማግሌውንና ጐበዙን ቈንጆይቱንም ሕፃናቶቹንና ሴቶቹን ፈጽማችሁ ግደሉ፤ ነገር ግን ምልክቱ ወዳለበት ሰው ሁሉ አትቅረቡ፤ በመቅደሴም ጀምሩ አላቸው። በቤቱም አንጻር ባሉ ሽማግሌዎች ጀመሩ።
7 ፤ እርሱም። ቤቱን አርክሱ፥ በተገደሉትም ሰዎች አደባባዮችን ሙሉ፤ ውጡ አላቸው። እነርሱም ወጥተው በከተማይቱ ገደሉ።
8 ፤ ሲገድሉም እኔ ብቻዬን ቀርቼ ሳለሁ በግምባሬ ተደፍቼ። ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! መዓትህን በኢየሩሳሌም ላይ ስታፈስስ የእስራኤልን ቅሬታ ሁሉ ታጠፋለህን? ብዬ ጮኽሁ።
9 ፤ እርሱም። የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ኃጢአት እጅግ በዝቶአል ምድሪቱም ደም፥ ከተማይቱም ዓመፅን ተሞልታለች፤ እነርሱም። እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቶአታል እግዚአብሔርም አያይም ብለዋል።
10 ፤ እኔም ደግሞ በዓይኔ አልራራም አላዝንምም፥ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ እመልሳለሁ አለኝ።
11 ፤ እነሆም፥ በፍታ የለበሰው የቀለም ቀንድም በወገቡ የያዘው ሰው። ያዘዝኸኝን አድርጌአለሁ ብሎ በቃሉ መለሰ።