ምዕራፍ 41

ወደ መቅደሱም አገባኝ፥ የግንቡንም አዕማድ ወርድ በዚህ ወገን ስድስት ክንድ በዚያም ወገን ስድስት ክንድ አድርጎ ለካ።
2 ፤ የመግቢያውም ወርድ አሥር ክንድ ነበረ፥ የመግቢያውም መቃኖች በዚህ ወገን አምስት ክንድ በዚያም ወገን አምስት ክንድ ነበሩ፤ ርዝመቱንም አርባ ክንድ ወርዱንም ሀያ ክንድ አድርጎ ለካ።
3 ፤ ወደ ውስጥም ገባ፥ የመግቢያውንም የግንብ አዕማድ ወርድ ሁለት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የመግቢያውም ወርድ ስድስት ክንድ ነበረ፥ የመግቢያውም ግንብ ወርድ በዚህ ወገን ሰባት ክንድ በዚያም ወገን ሰባት ክንድ ነበረ።
4 ፤ በመቅደሱም ፊት ርዘመቱን ሀያ ክንድ ወርዱንም ሀያ ክንድ አድርጎ ለካና። ይህ ቅድስተ ቅዱሳን ነው አለኝ።
5 ፤ የመቅደሱንም ግንብ ስድስት ክንድ አድርጎ፥ በመቅደሱም ዙሪያ ሁሉ ያሉትን የጓዳዎቹን ሁሉ ወርድ አራት ክንድ አድርጎ ለካ።
6 ፤ ጓዳዎቹም አንዱ ከአንዱ በላይ በሦስት ደርብ ነበሩ፥ በእያንዳንዱም ደርብ ሠላሳ ጓዳዎች ነበሩ። በመቅደሱም ግንብ ዙሪያ ደገፋዎች ይሆኑ ዘንድ አረፍቶች ነበሩ፥ በመቅደሱም ግንብ ውስጥ ደገፋዎች አልነበሩም።
7 ፤ በቤቱም ዙሪያ ባለ ግንብ ውስጥ በነበሩት አረፍቶች ምክንያት ላይኞቹ ጓዳዎች ከታችኞቹ ጓዳዎች ይበልጡ ነበር፤ ከታችኛውም ደርብ ወደ መካከለኛው ከመካከለኛውም ደርብ ወደ ላይኛው የሚወጣበት ደረጃ ነበረ።
8 ፤ ለመቅደሱም ከፍ ያለ ወለል በዙሪያው እንዳለው አየሁ፤ የጓዳዎቹም መሠረት ቁመቱ ሙሉ ዘንግ የሚያህል ስድስት ትልቅ ክንድ ነበረ።
9 ፤ የጓዳዎቹም የውጭው ግንብ ውፍረት አምስት ክንድ ነበረ፤ በመቅደሱም ጓዳዎች አጠገብ የቀረ አንድ ባዶ ስፍራ ነበረ።
10
11 ፤ በዚህም በባዶው ስፍራ አንዱ በሰሜን በኩል አንዱም በደቡብ በኩል የጓዳዎች መግቢያ ነበረ የባዶውም ስፍራ ወርድ በዙሪያ አምስት ክንድ ነበረ። በመቅደሱም ዙሪያ ወርዱ ሀያ ክንድ የሆነ ልዩ ስፍራ ነበረ።
12 ፤ በምዕራብም በኩል በልዩ ስፍራ አንጻር የነበረ ግቢ ስፋቱ ሰባ ክንድ ነበረ። በግቢውም ዙሪያ የነበረ ግንብ ውፍረቱ አምስት ክንድ ርዝመቱም ዘጠና ክንድ ነበረ።
13 ፤ የመቅደሱንም ርዝመት መቶ ክንድ፥ የልዩውን ስፍራና ግቢውን ከግንቡ ጋር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
14 ፤ ደግሞም በምሥራቅ በኩል የነበረውን የመቅደሱንና የልዩውን ስፍራ ወርድ አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
15 ፤ ወደ ኋላውም ባለው በልዩ ስፍራ አንጻር የነበረውን የግቢውን ርዝመት በዚህና በዚያም ከነበሩት ከግንቦቹ ጋር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
16 ፤ መድረኮቹ፥ መቅደሱና በስተ ውስጥ ያለው ክፍል ደጀ ሰላሙም በእንጨት ተለብጠው ነበር፥ በሦስቱም ዙሪያ የዓይነ ርግብ መስኮቶች ነበሩ። መቅደሱም በመድረኩ አንጻር ከመሬት ጀምሮ እስከ መስኮቶቹ ድረስ በእንጨት ተለብጦ ነበር፤ መስኮቶቹም የዓይነ ርግብ ነበሩ፤
17 ፤ በደጁም ላይ እስከ ውስጠኛው ክፍል ድረስ፥ በውጭም ግንቡ ሁሉ ውስጡም ውጭውም ተለብጦ ነበር።
18 ፤ ኪሩቤልና የዘንባባው ዛፎች ተቀርጸውበት ነበር፤ የዘንባባውም ዛፍ ከኪሩብና ከኪሩብ መካከል ነበረ፤ ለእያንዳንዱም ኪሩብ ሁለት ፊት ነበረው።
19 ፤ በአንድ ወገን ወዳለው የዘንባባ ዛፍ የሰው ፊት ይመለከት ነበር፥ በሌላውም ወገን ወዳለው የዘንባባ ዛፍ የአንበሳ ፊት ይመለከት ነበር፤ በቤቱ ሁሉ ዙሪያ እንደዚህ ተደርጎ ነበር።
20 ፤ ከመሬት አንሥቶ እስከ ደጁ ራስ ድረስ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር። የመቅደሱ ግንብ እንደዚህ ነበረ።
21 ፤ የመቅደሱ መቃኖችም አራት ማዕዘን ነበሩ፥ የመቅደሱ ፊትም መልኩ እንደ ሌላው መልክ ነበረ።
22 ፤ መሠዊያውም ቁመቱ ሦስት ክንድ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ወርዱም ሁለት ክንድ ሆኖ ከእንጨት ተሠርቶ ነበር፤ ማዕዘኖቹም እግሩም አገዳዎቹም ከእንጨት ተሠርተው ነበር፤ እርሱም። በእግዚአብሔር ፊት ያለችው ገበታ ይህች ናት አለኝ።
23 ፤ ለመቅደሱና ለተቀደሰው ስፍራ ሁለት መዝጊያዎች ነበሩአቸው።
24 ፤ ለእያንዳንዱ መዝጊያም ሁለት ተዘዋዋሪ ሳንቃዎች ነበሩት፤ ለአንዱ መዝጊያ ሁለት ለሌላውም መዝጊያ ሁለት ሳንቃዎች ነበሩት።
25 ፤ በግንቡም ላይ በተቀረጹት ዓይነት በእነዚህ በመቅደሱ መዝጊያዎች ላይ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር፤ በስተ ውጭም ባለው በደጀ ሰላሙ ፊት የእንጨት መድረክ ነበረ።
26 ፤ በደጀ ሰላሙም በሁለቱ ወገን በዚህና በዚያ የዓይነ ርግብ መስኮቶችና የተቀረጹ የዘንባባ ዛፎች ነበሩበት፤ የመቅደሱም ጓዳዎችና የእንጨቱ መድረክ እንዲሁ ነበሩ።